Uncategorized

ሁሉም የሕሊና እስረኞች ይፈቱ !!!

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለአገር ማሰብ፣ ለመብት መቆም፣ “አንዲት ኢትዮጵያ” ማለት ወንጀል የሆነበት ኢትዮጵያ ናት። ብርቅዬ የተማሩ፣ ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች የሚያስቡ ልጆቿ ወደ ወህኒ የሚወረወሩባት አገር ናት። አሳዛኝ አገር ሆናለች።ሆኖም ተስፋ የሚሰጡ ብዙ ነገሮች እየታዩ ነው። አንዱዋለም አራጌ ቢታሰርም፣ እጅግ በጣም ብዙ አንድዋለም አራጌዎች ፈርተዋል። እንደ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አንጋው ተገኝ፣ ገበየሁ ሲሳይ፣ ስንትየሁ ቸኮል፣ ሃዲያ ሞሃመድ፣ መሳይ ተኩ ..የመሳሰሉ የአንድነት ሰዎች አንዱዋለም አራጌን በወህኒ ተቀላቅለዋል። ሆኖም ሌሎች ብዙ ከየቦታው እየተነሱ ነው። ታጋይ ቢታሰር ትግል አይቆምም። ጥቂቶችን በማሰር የነጻነትና የለዉጥ ጥያቄን ማፈን አይቻልም።በመሆኑም ከአንዱዋለም አራጌ ጎን እንቆማለን። አላማው አላማችን ነው። እነርሱን “ሽብርተኛ” ቢሉትም ለኛ ወንንድማችን፣ ጀግናች፣ መሪያችን ነው። እኛም አንዱዋለም አራጌዎችን ነን። እርሱ በአካል ድምጹን ማሰማት ባይችልምም፣ እኛ እርሱን ሆነ የነጻነትና የፍትህ ድምጽ እንደ መብረቅ እናስተጋባለን።አንድዋለም አራጌና ሌሎች ጀግኖቻችን በሙሉ እስኪፈቱ፣ አገራችን ኢትዮጵያም ራሷ እስክትፈታ ትግሉ ይቀጥላል!

ይችን ያልተዘመረላትን ሴት እናውቃታለን ? የሚሊዮኖች ድምጽ

ያልተዘመረላት፣ ያልተነገረላት ጀግና ኢትዮጵያዊት ሴት ናት። እንዴሌሎች “እኔ ምን አገባኝ ? አርፌ ልቀመጥ” ብላ፣ ባርነትንና ዉርደትን አሜን ብላ ተቀብላ፣ ሕሊናዋን ሸጣ፣ የገዢው ፓርቲ አዉደልዳይ ሆዳም ካድሬና አገልጋይ ሆና ፣ በዘረኘንትና በጠባብነት በሽታ ተለክፋ መኖር ትችል ነበር። ግን አላደረገችውም።]

ከደቡብ ክልል ከወላይታ ሶዶ ናት። ሃይለማሪያም ደሳለኝ መጣሁበት ካለው። እንደ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሌሎች አሽከር አልሆነችም። እንደ ኃይለማሪያም ደሳለኝ አልተንቦቀቦቀችም። እንደ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሕሊናዋን አልሸጠችም። የወላይታ ጀግና የሆነውን የንጉስ ጦናን ወኔ ተላብሳ፣ ለእዉነት፣ ለፍትህ፣ ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲና ለኢትዮጵያ አንድነት ቆመች። የወላይታ ሕዝብ በባህሉ፣ በቋንቋም በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ምብቱ ሲደፈር የማይወድ፣ ታታሪ ሕዝብ ነው። ይች ሴት በትክክል የወላይታ ሕዝብን አቋም አንጸባረቀች። ሕገ መንግስቱ በሚፈቅደው የመደራጀት መብት መሰረት ፣ መብቷን ለማስከበር፣ የአንድነት ፓርቲን ተቀላቀለች። የወላይታ ዞን የአንድነት አመራር አባል ሆነች።

የአንድነት ፓርቲ ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መርህ በወላይታ ዞን ሕዝባዊ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት፣ የቅስቀሳ ወረቀቶችን ለሕዝቡ ሳትፈራ ታድል ነበር። ያኔ ገዢዎች አሰሯት። ብዙ ጊዜ በፍርድ ቤት ካንገላቷትና ካሰቃይዋት በኋላ፣ ያለ አንዳች መረጃ፣ በአካባቢ የደህንነት ሃላፊ መመሪያ “አመጽ ቀስቃሽ” ተብላ ተፈረደባት። ወደ ወህኒ ተወረወረች። ያልተዘመረላት የነጻነት ታጋይ ጀግናዋ ሃዲያ ሞሃመድ !!!!

ኢትዮጵያዉያን በየቦታው በአይምሯችን ላለፉት 20 አመታት፣ ወያኔዎች የቀረቀሩትን፣ ስለነርሱ ያለንን የዉሸት ምስል፣ ከአይምሯችን አውጥተን፣ ምንም ጉልበትና አቅም የሌላቸው ደካሞችና የበሰበሱ መሆናቸውን ተገንዝበን፣ እንደ ሃዲያ ሞሃመድ፣ እንደ ርዮት አለሙ፣ እንደ ንግስት ወንዳፍራ፣ እንደ ሜሮን አለማየሁ ….ብንነሳ የአገራችንን ትንሳኤ እናፋጥነው ነበር። ሰቆቃችን እንዳይራዘም፣ ዉርደታችን::

እነርሱ ሽብርተኛ ይሉታል፣ እኛ ግን ጀግና እንለአለን – አማኑኤል ዘሰላም

የአንዲት ትሁት ኢትዮጵያዊት ባላቤትና የልጅ አባት ነዉ። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ወጣት አመራር አባል ነበር። በፓርቲዉ ዉስጥ፣ በዉጤት ላይ የተመሰረተ፣ የሰለጠነ ሰላማዊ ፖለቲካ ያራምድ የነበረውን በወያኔ ሕጋዊነትን በጉልበት የተነጠቀ የአንድነት ፓርቲ አደራጅ ነበር። በሐሰት የሽብርተኝነት ክስ ይከሰሳል። ምንም እንኳን በአገራችን የሕግ ስርዓት እንደሌለ ቢታወቅም፣ የአገዛዙን ሕገ-አራዊነትን ለማጋለጥ ሲል፣ ራሱን ለመከላከል ሞከረ። ሕግን በማመዛዘን ሳይሆን ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮ በተሰጠ የፖለቲካ መመሪያ መሰረት፣ ከሌሎች የትግል አጋሮቹ ከነአንዱዋለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ ከመሳሰሉት ጋር፣ ጥቁር ካባ በለበሱ ዳኛ ተብዬ ካድሬዎች በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ። የ18 አመታት እስራት ተበየነበት። ይህ ወጣት ናትናኤል መኮንን ይባላል።

የተከሰሰበት ችሎት ይሰማ በነበረ ወቅት፣ ናትናኤል መኮንን በፍርድ ቤት ከተናገራቸው የተወሰኑትን፣ አንባቢያን ምን ያህል የተከበረ፣ ትልቅ እና አስተዋይ መሪ ፣ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዉያን እንዳለን ይረዱ ዘንድ፣ እንደሚከተለው አቅርበናል፡
«ክቡር ፍ/ቤት፡- እኔ እንኳን ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር ስለመግደል ላሴርና የህዝብ ሀብት፣ የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ስለማውደም ላቅድ ቀርቶ አፈናን፣ ጭቆናንና ግፍን በሰላማዊ መንገድ ከመታገልና ከመቃወም ውጭ የገዥውን ፓርቲ አባላትና አመራሮች እንኳን በጥላቻ ዓይን ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ወደፊትም አልመለከታቸውም፡፡ ነገር ግን በፅናት አምርሬ እታገላቸዋለሁ፡፡ አፈናቸውን እንዲያቆሙ ከቁልቁለት ጉዟቸው እንዲመለሱ፤

ክቡር ፍ/ቤት፡- ሽብር የእኔ መገለጫ አይደለም፡፡ አገዛዙ እንዳለው እኔ ባለስልጣናትን ለመግደልና የህዝብ ሀብት የሆኑትን መሰረተ ልማቶች ለማውደም ያሴርኩ፣ ያቀድኩና በሽብር የተፈረጀ ድርጅት አባል ያልሆንኩና ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ሁኔታ ላይ ካለው የሻዕቢያ መንግስት ጋርም የተባበርኩ ሳልሆን በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ መስራችና የም/ቤት አባል ለአንድነት አላማዎች ተፈፃሚነት በቁርጠኝነት የምታገል፣ እንኳን ከሻዕቢያ ጋር ልተባበር፡- ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ሀገሬን የባህር በር ያሳጣትን ወያኔን የምታገል ለሀገር አንድነትና ክብር የምታገል፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ።

ክቡር ፍ/ቤት፡- አሁን በአገዛዙ እየተወሰዱ ያሉት የእስር እርምጃዎች ዋነኛ ምክንያት ሽብር ስለተሞከረ፣ ወይም ስለታቀደ፣ ወይም ደግሞ የሻዕቢያ ተላላኪ ስለተገኘ ሳይሆን ዜጐች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚያቀርቧቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ማዳፈን ነው፡፡ እስሩ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ባለች ሀገራችን ለምን ራበን /ለምን ኑሮ ተወደደ/ ትላላችሁ ነው፡፡ ለምን የነፃነት ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእስሩ ምክንያት ለምን እኔ የምላችሁን ብቻ አትቀበሉም ነው፡፡ ለምን የለውጥ ጥያቄ ታነሳላችሁ ነው፡፡ የእሥሩ ምክንያት በአረብ አገራት የለውጥና የነፃነት ንፋስ ወደ አቶ መለስ አገዛዝም እንዳይመጣ የተወሰደ የመከላከል እርምጃ ነው።»

በሽብርተኝነት ወንጀል ጥፈተኞች በተባለ ጊዜ ናትናኤል ከተናገረዉ የሚከተለዉ ይገኝበታል፡
«እኔ አቶ ናትናኤል መኮንን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ቤት አባልና መስራች፣ የወረዳ 2 እና 14 ሰብሳቢ /አደራጅ/፣ በሰላማዊ ትግል የማምን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲራብ ተርቤ፣ ሲጠማ ተጠምቼ፣ ሲገረፍ ተገርፌ፣ እስሩንም መከራውንም ከህዝቤ ጋር እየተቀበልኩ ለዴሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ከሌሎች ሰላማዊ ታጋዮች ጋር በመሆን በፅናት እያካሄድኩ ያለሁ፣ ከችግሩ ባለቤት ከኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍና አጋርነት በስተቀር የማንንም ድጋፍ የማልፈልግና የማንንም ፍላጐት የማላስፈፅም፣ የሀገሬን ጥቅም በምንም ሁኔታ አሳልፌ የማልሰጥ፣ ኃላፊነት የሚሰማኝ፣ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል ነኝ፡፡ አዎ እኔ የግንቦት ሰባት አባል ሳልሆን የአቶ መለስ ረጅም አገዛዝና ጭቆና በቃኝ ያልኩ የሻዕቢያ ተላላኪ ሳልሆን ለነፃነቴ መታገል የምችል፣ ነፃነቴን እስከ ሞት ድረስ የወደድኩ ኩሩ ኢትዮጵያዊና የአንድነት አባል እንጅ ሽብርተኛ፣ የሻዕቢያ ተላላኪና የግንቦት ሰባት አባል አይደለሁም፡፡

አያቶቼ እንዳስተማሩኝ ኢትዮጵያዊነት የርህራሔ፣ የኩራትና የነፃነት ምልክት እንጅ የጭካኔ፣ የባርነትና የውርደት ምልክት አይደለም፡፡ ስለዚህ የጭካኔ ምልክት የሆነው ሽብር ፈፃሚም አስፈፃሚም አይደለሁም፡፡ ወደፊትም አልሆንም፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ከድርጅቴ ከአንድነት ጋር በመሆን በፅናት የትም፣ መቼም፣ በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እቀጥላለሁ»

እነርሱ ናትናኤልን «ሽብርተኛ» ይሉታል። እኛ ግን ይህንን አንጋፋ ሰው ጀግናችን የሚል ስያሜ ሰጥተነዋል። እነርሱ ዜጎችን ማዋረድ፣ ማሰር፣ ማሰቃየትና ማሸበር ያስደስታቸዋል። እኛ ግን ድምጻቸውን ማሰማት ለማይችሉ ፣ በግፍ ለታሰሩ፣ ለነ ናትናኤል መኮንን እንቆማለን።

እነርሱ ያሸነፉ ይመስላቸዋል። ነገር ግን፣ እስረኞችን ለመፍታትና ሌሎችን ላለማሰር ባልወሰኑ ቁጥር፣ ተቀባይነታቸው እየወደቀ፣ የበለጠ ጠላቶች እያፈሩ፣ የዲፕሎማቲክም ሆነ የአገር ዉስጥ ፖለቲካ ኪሳራ እያጋጠማቸው፣ ወደ ዉድቀት እያመሩና እየተዋረዱ ያሉት፣ እነርሱ እራሳቸው መሆናቸውን እንነግራቸዋለን።

ንዱዋለም አያሌው የአንድነት አመራር አባል ነው። ከአንዱዋለም አራጌ፣ ናአትናኤል መኮንን እና ሌሎች እስረኞች ጋር ኔብር አገሩን እና ሕዝቡን በመዉደዱ፣ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም በመቆሙ፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ በመጮሁ ሽብርተኛ ተብሎ ወደ ወህኒ የወረደው።
አንዱዋለም አያሌዉና ሁሉም የሕሊና እስረኞች እስኪፈቱ ትግሉ ይቀጥላል።

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Blog Stats

  • 52,481 hits
Advertisements
%d bloggers like this: