Uncategorized

ኢትዮጵያ ታሪክ ቅሚያና የዘርኝነት ሴራ – ደ .ሰርጸ ደስታ

ብዙ ጊዜ አስቤዋለሁ ግን መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ነው፡፡ ብዙዎች ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት ሊያወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ታላቅነታችን በምንድነው; ከዚህ በታች የማሳርፈው ሐሳብ ሁሉ የራሴ አስተያየት ነው፡፡ ምንዓልባት የሚቀየም ካለ ከልቤ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ሰዎች ይገባቸው ይሆን በምለው ፊት ለፊት የሆኑ ቃላት ልጠቀም ስለምችል አሁንም ከምንም አንጻር ሳይሆን እኔን ስለመሰለኝ ነው፡፡ ከተስማማችሁ መልካም ስህትት ሆኖ ካገኛችሁት ግን ተሳስተሀል የምታስበው ትክክል አይደለም ብሎ ሊያርመኝና እኔም ያላወቅኩትን ሊያስተምረኝ የሚችል ካለ ከልብ እቀበላለሁ፡፡

  1. የጥንታዊው ስልጣኔና ታሪክ ቅሚያ፡

በእኔ አስተሳሰብ ጥንታዊ ስልጣኔ ታይቶበት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ያለንው ሕዝቦች (ይቅርታ የሕዝብ በራሱ ብዙ እንደሆነ አሳምሬ አውቀዋለሁ የዘመኑ ቋንቋ ስለሆነ ነው) የማንነታችን መገለጫ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ አክሱምም የትግሬ ላሊበላም የአማራ ሌላም በሉት አሁን ባለቤት እንደሆኑ የሚያስቡት ወገኖች አባቶቻቸው የሰሩት ሳይሆን የሌላ ሕዝብ በረከት እንደሆን አምናለሁ፡፡ ይህንንም ከልጅነቴ ጀምሮ አስተውለዋለሁ፡፡ ደግነቱ ግን ከውጭ በመጣ ሳይሆን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አካል ሆኖ ባለ ሕዝብ እንደተሰራ ሳስብ እጽናናለሑ፡፡ የቀደመው የአክሱምም በሉት የኋለኛው የላሊበላ አስደናቂ የሰው ልጆች ጥበብ የኢትዮጵያውያን መጀመሪያ ነዋሪዎች የሆኑት ዛሬ አገው ብለን የምንጠራው ሕዝብ ታሪክ ነው፡፡ የዚሕ ሕዝብ ታላቅነት ደግሞ በኢትየጵያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን የጥንታውያኑ ግብጾችም ታሪክ ባለቤት ነው፡፡ ፈርዖኖችና አክሱማውያን ወይም ዛሬ እኛ አገው የምንለው ሕዝብ አንድ ወገን እንደሆኑ እንገነዘባለን፡፡ ይህ ሕዝብ ግን ዛሬ በግብጽ በአረቦች በኢትዮጵያ ደግሞ ራሳቸውን ሰሎሞናውያን ነን በሚሉ ወገኖች ታሪኩ ተነጥቋል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎችም ይህን ጥንታዊ መሠረት የነበረውን ሕዝብ ታሪክ ከመዘከር ይልቅ የኢትየጵያን ጥንታዊ ጥበብ ያመከነውን ራሱን ሴማዊና የሰሎሞን ዘር እያደረግ የሚመጻደቀውን ሕዝብና መሪዎች ታሪክ ታላቅነት ሊነግሩን ብዙ ጥረዋል፡፡

ጥቂት እውነታዎችን እናንሳ በጥናዊቷ ኢትዮጵያ (አቢሲኒያ) (ምሳ. አክሱም፣ አዱሊስ)፣ ምስር (ግብጽ)፣ ኑቢያ (ሱዳን) ተንሰራፍቶ ይኖር የነበረው ይህ ነገድ (ወገን) በታላቅነቱ አለምን ያሰፈራና፣ ያስገርም እንደ ነበር ጥንታውያኑ የታሪክ ጸሐፊዎች መዝግበውታል፡፡ ከነዚህም አንዱ ዲዎከራተስ የተባለው ግሪካዊ ጸሐፊ ከክርስቶስ ልደት በፊት መዝግቦት ያለው ታሪክ ነው፡፡  ይህ ወገን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአክሱምና አዱሊስ ታላቅና መሪ ሆኖ ሳለ የሰሎሞን ወገን ነን በሚሉና አረቦች ቀስ እያለ በመዳከሙ ስልጣኑ ስሎሞናውያን ነን በሚሉ እጅ ገባ፡፡ አዱሊስን ቀደም ብሎ በጦርነት አጣት አክሱምንም ለቀቀ፡፡ ለዘመናት ደንታ ቢስና የጥበብ አውዳሚ በነበረው የሰሎሞን ወገን ነኝ በሚለው አካባቢው ሲመራ ከቆየ በኋላ እንደገና ወደ ደቡብ በማፈግፈግ ዛሬ ላሊበላ ወይም ሮሃ የምትባለውን ቦታ ማዕል በማድረግ ያ የጥንቱ ባለታሪክ ሕዝብ ጉልበት አግኝቶ ሥልጣን ያዘ፡፡ ብዙዎቻችን ይህን ታሪክ የዛግዌ ሥርዎ መንግስት እያልን በትምሕርት ቤት ተምረንዋል፡፡ አስተማሪዎቻችን ግን የአክሱምን ታሪክ ከሰሎሞናውያኑ ጋር አጣምረው ነው የነገሩን፡፡ አዎ ታሪክን በመቀማት የተገኘ ታሪክ የመጀመሪየው የአክሱም ሰሎሞናዊ ለተባለው የጥበብ ጠላት መሰጠቱ ነው፡፡

ይህ ጥንታዊው የኢትየጵያ ሕዝብ እንደገና ሌላ ታሪክ በሮሃ (ዛሬ ድረስ አለምን የሚያስደምመውን) እያሳየ ሳለ ነገሮች ግራ በሚያጋባ ሆኔታ በሀይማኖት በሚመስል ማግባባት ሥልጣኑን አሳልፎ ሰሎሞናዊ ነኝ ለሚለው ወገን ሰጠ፡፡ የመጀመሪያውም ሰሎሞናዊ ነጋሲ ይኩኖ አምላክ ይባላል፡፡ ልብ በሉ ይህ ሕዝብ ሥልጣን አሳልፎ የሰጠው በሐይማኖታዊ ጉዳይ ስለነበር በሠላም ነው፡፡ ዛግዌዎች (አገዎች) እጅግ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ስለነበርም በዚህ ጉዳይ የተታለሉ ይመስለኛል፡፡ ይቅርታ እዝህ ጋር ያለው ሒደት ሐይማኖታዊ ጉዳይ ስላለው ግር ስላለኝ ብዙ መናገር አልፈለገኩም፡፡ የተሳሳትኩትም ካለ ሒደቱን አጥርቶ የሚያውቅ ሊያብራራልን ይችላል፡፡ እዝህ ጋር ግን መጥቀስ የምፈለገው ሥልጣኑን ለሰሎሞናውያኑ ሲያስረክብ የተገባለት የራስ ገዥነት ቃል ኪዳን ስለነበር ልብ ትሉት ዘንድ የአገው ገዥዎች እስከ አጼ ኃለስላሴ ዘመን ድረስ ዋግ ሹም የሚል ልዩ መጠሪያ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ እንደ ውሉ ዋግ ሹም እንደ ራሶቹ ለንጉሱ የመታዘዝ ግዴታ የለበትም የመስማማት እንጂ፡፡

እንግዲህ ከይኩኖ አምላክ ጀምሮ ኢትየጵያን አንደገና አንድ ለማድረግ እስከተንቀሳቀሱት የአጼ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምኒሊክ ታሪክ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ታሪክ ምን እነድሚመስል ሁላችሁም ትረዱታላችሁ፡፡ ሰለሞናውያኑ ለሁለሁለተኛ ጊዜ እድል ቢያገኙም አገሪቷን በየጎጡ ከፋፍለው በሚገዙ የዘመናታ ዱርዬ መሳፍንቶች መፈንጫ አደረጓት፡፡ በታሪክም ይህ ዘመን የጨለማው ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህን እውነት አጉልቶ የሚነግረን የታሪክ ተመራማሪ አላገኘንም፡፡ አሁንም በዛው በተለከፍንበት የዘመናት ዝቅጠት በሆነው አስተሳሰብ እንዳክራለን፡፡ እዚህ ድረስ ያለውን አንኳር ታሪክ ከጠቆምኩ ይበቃኛል፡፡ ብዙ ማተት ይቻላል ውስጡን አለማወቅ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ተሳስተሀል የሚል ያርመኝ

  1. የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ታሪክ ባለቤትነት ማሳጣትና ትውልድን በዘረኝነት ማምከን፡-

ይህ ታሪክ በአጼ ቴዎድሮስ ኋላም በዩሐንስ ተሞክሮ እውን የሆነው ግን በታላቁ ምኒሊክ ነው፡፡ እዚህ ታሪክ ላይ ዛሬ ያለው ትውልድ ብዙ የተመሰቃቀለ አመለካከት ስላለው በእርጋታ አንብቦ ከተረዳኝ በኋላ የምናገረው እውንት ካልሆነ በተጨባጭ ማስረጃ ያርመኝ፡፡ ይህ ታሪክ በይበልጥ ያሳተፈው ሕዝብ የትኛውን ነበር; በዚህ ታሪክ ሒደት ውስጥ ታሪክን የተቀማ ሕዝብ አለ; ከላይ ያነሳሁት የአገው ሕዝብ ታሪኩን በጉልበት ማጣት ተቀማ እንጂ ታሪኩን የራሱ እንደሆነ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በጎንደር አካባቢ እኛ የተለየን ነን ብሎ የተነሳው የቅማንት ሕዝብም ጥያቄ ከዚሁ መሠረት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ብዙም ጠለቅ ብዬ ስለማላውቅ ግን ለመጠቆም ያህል እነጂ የምሰጠው መረጃ የለኝም፡፡ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ግን ከፍተኛ አስተዋጾ የነበረው ሕዝብ  ታሪኩን መቀማት ብቻ ሳይሆን የአንተ አይደለም ተብሎ ከነጭርሱ የራሱን ታሪክ እንዲጠላና የጠላት ታሪክ እንድሆነ እንዲያስብ ተደርጓል፡፡

ወደዚህ ዝርዝር ከመገባቴ በፊት አንድ ቁም ነገር አዘል ተረት ትዝ ስላለኝ ላነሳው ወደድሁ፡፡ ሰወዬው በግ ተሸክሞ ገበያ ሊሸጥ ይሄዳል ሶስት ሌቦች ሰውዬውን በጉን ሊነጥቁት አስበው ተማከሩ፡፡ ምክራቸውም በተለያየ ቦታ መንገድ ላይ ሆነን በግ ሳይሆን ውሻ እንደተሸከመ ብንነግረው በጉን ይጥልልናል ብለው ተማከሩ እንደ ተማከሩትመ በተለያየ ቦታ ሆነው ገበያው መንገድ ላይ ይጠብቁት ጀመር፡፡ የመጀመሪያው ገና ባለበጉ ከሰፈሩ ወጥቶ የገበያውን መንግድ ሲጀምር ያገኘውና አያ እከሌ ምነው በዛሬው ቀን ውሻ ተሸክመህ ወዴት ትሄዳለህ ይለዋል፡፡ ባለበጉ ተናዶ እንዴ ወሻ ተሸከምክ ትለኛለህ ብሎ ሌባውን ዘልፎት ይሄዳል፡፡ መሀል መንገድ ላይ ሲደርስ ሌላው ሌባ ያገኘውና ከመጀመሪያው በባስ ምነው አያ እከሌ በገበያ ቀን ውሻ ተሸከመህ ወዴት ነው ይለዋል፡፡ ሰውይው ትንሽ መጠራጠር ጀመረ ግን ይሄንንም አልፎት ሄደ፡፡ ሶስተኛው ገበያው አቅራቢያ ሊደረስ ሲል ያገኘውና ራሱን ይዞ አቶ እከሌ ምነው በሠላም ነው በገበያ ቀን ውሻ ተሸክመሕ የመጣህው ይለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰውዬው የተሸመው በግ ሳይሆን ውሻ እንደሆን ስላመነ ከትከሻው አውርዶ በጉን ይለቀዋል፡፡ ሌቦቹ በጉ የሄደበትን ተከትለው በዚህ ሁኔታ በጉን ይወስዱበታል፡፡ የኋለኛው የኢትየጵያ ታሪክ ቅሚያም እንዲሁ ነው፡፡

ከላይ በጠቀስኩት ተረት መሰል ቁምነገር አይነት የገዛ ታሪኩን በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ተነጥቆ እንደዜጋ እንኳን ሳይሆን እንደ ባዕድ ራሱን እንዲቆጥር የተደረገው ሕዝብ በዘመናዊኞቹ የኦሮሞ ሕዝብ እየተባለ የሚጠራው የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ነው፡፡ ከይቅርታ ጋር እዚህ ጋር የኦሮምኛ ተናጋሪ እንጂ ኦሮሞ የሚለውን ለመጠቀም አልፈለግኩም፡፡ ስለዝህ ጉዳይ ብዙ ራሱን በቻለ ርዕስ የማነሳው ይሆናል፡፡ ቢቻል በሌላ ፅሑፍ፡፡ ወደ ተነሳሁበት ልመልሳችሁ፡፡ የዘመናዊቷ ኢትየጵያን የፈጠሩት ምኒሊክ እንደሆኑ ሁላችንም የማንክደው ሀቅ ነው፡፡ የምኒሊክ ታሪክ ደግሞ ዋነኛ ተዋናዮቹ እነማናቸው ቢባል የኦሮምኛ ተናጋሪው በተለይም የሸዋ ኦሮሞ ታሪክ ነው፡፡ አስቀድሞ አገርን እንደ ከማድረግ ጀምሮ አፍሪካን ብሎም የጥቁርን ሕዝብ ሁሉ ታሪክ የለወጠው የአደዋው ታሪክ ይህ ታላቅ ሕዝብ በመሪነት የተሳተፈበት ድል ነው፡፡

የአገር አንድ ማድረጉን ሂደት ዛሬ ድረስ አስከሚኮነነው የአኖሌና ጨለንቆን ጦርነት ጨምሮ በኋላ ልምጣበት ግን እስኪ ሁላችንም ለሂሊናችን ዳኝነት ይረዳን ዘንድ በአደዋ ልጅምር፡፡ በአደዋው ድል ከሚታወቁ ጀግኖች ፊታውራሪ ገበየሁ ጎራና ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ተወዳዳሪ የሚገኝላቸው አይመስለኝም፡፡ ከነጭረሱም ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ራሳቸውን መስዋዕት ባያደርጉ ጦርነቱ ሽንፈት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ስናገር ብዙዎች የሚረዱት ስላልመሰኝ እያዘንኩ ነው፡፡ ገበየሁ የሚመሩት ጦር የመጀመሪያው ነበር፡፡ ጦሩ ከጣሊያን ጋር ሊገጠም ፈራ፡፡ ከዚህ በኋላ ገበየሁ ጦሩን በማዘዝ ሳይሆን እንዲህ የሚል ቃል ተናገሩ፡፡ “ሁላችሁም ተመለሱ ለምንሊክ ገበየሁ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በጣሊያኖች ተገደለ ብላችሁ ንገሩት” ብሎ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ገሰገሰ፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር ወታደሩ የመሪያቸውን ቁረጠኛ ውሳኔ ሲያውቅ ፍርሀቱ ለቆት ጦርነቱን ከመሪው ጋር የተጋፈጠው፡፡ ይህ የታሪክ እውነት ነው! ይህ ባይሆን የአደዋ ጦርነት ምን ሊሆን እንሚችል ገምቱ፡፡ አደዋ የገበየሁ ደም ውጤት ነው፡፡ ስለ ገበየሁ ግን የረባ ታሪክ እንኳን አንብቤ አላውቅም፡፡ አባቴ ከነገረኝ በቀር፡፡ እንዳ ስላሴን ጣሊያን አረከሰው ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፣ የምትለው ስንኝ ግን በጣም ታስደስተኛለች፡፡ አደዋ የብዙዎች ተሳትፎ ቢኖርበትም እኝህ ታላቅ ሰው መስዋዕት ባይሆኑ ግን ታሪኩ ሌላ መልክ ሊኖረው እንሚችል አስባለሁ፡፡ በገበየሁ ሞት ጦሩ ሁሉ በእልህና በቆራጥነት ይዋጋ ነበርና፡፡ ሌላው በተለምዶ ባልቻ አባ ነብሶ የምንላቸው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በአደዋው ጦርነት በቀዳሚነት የሚታወቁት ጀግና ናቸው፡፡ ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ …. የሚባለውም ከገበየሁ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጀግንነት ባሕሪ ስለነበራቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ባልቻ ሳፎ በመጀመሪያው ጦርነት ወጣት ስለነበሩ ሁለቱንም የኢጣሊያ ጦርነት የተሳተፉ ሰው ናቸው፡፡ የሞቱትም በሁለተኛው ጦርነት ነው፡፡ ቅድም ኦሮሞ የሚባለው ሕዝብ በደም ይሁን በቋንቋ ለእኔ ግልጽ ስላለሆነልኝ ነው፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልኩት፡፡ ቋንቋ ባደግንበት ነውና፡፡ ኦሮሞ የሚባለው ሕዝብ እንደ አንድ መንደር ነዋሪ አይደለም፡፡ በጣም ውስብስብ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እነ ራስ ሚካኤል የወሎው (ራስ አሊ መሰለኝ ይቅርታ አርሙኝ)፣ ራሳቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሌሎችም የዚሁ የአደዋውና የምኒሊክ ዘመን ታላቅ ባለታሪኮች ከዚሁ ሕዝብ አካል ናቸው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ የአደዋ ታሪክ በቀዳሚነት ሊዘከር የሚገባው ከዚህ ሕዝብ ጋር ነው፡፡ እውነት እንናገር ከተባለ ከትግራይ ራስ አሉላና መሪም ስለነበረሩ ራስ መንገሻ ዩሐንስ በቀር እዛ ቦታ ታሪኩ የሚታወቅ ሰው አልሰማሁም፣ አማራ ከሚባለውም ሕዝብ ከንጉስ ተክለሀይማኖት (ንጉስ ተክለሀይማኖትም ምን አልባት አማራ የሚባለው ሕዝብ አካል ከሆኑ ማለት ነው) በቀር ማን ተሳታፊ እንደነበር አላውቅም፡፡ እንግዲህ አማራ የተባለው ሕዝብ ተሳተፈ ከተባለ ራሳቸው ሚኒሊክና አጎታቸው ራስ መኮንን ናቸው፡፡  ይህም ባይሆን የሁለቱም መሪዎች ወታደሮች ኦሮሞ የሚባለው ሕዝብ ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ እያሰብን፡፡  ለነገሩ ራሳቸው ምኒሊክ ሆኑ መኮንን የዘር (በደም ከሆነ) ሀረጋቸው ከየት እንደሆነ ማን ያውቃል; ሸዋ እንሆነ የተወሳሰበ ሕዝብ ነው፡፡ ይህን ታሪክ እንዲክድና እንሁም እንዲጠላው የተደረገው የዛሬው የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ትውልድ ለዚህ ባይተዋር ለአገሪቱም እነደዜጋ እነዳያስብ ሆኗል፡፡ ራስ መኮኒን የወልደ ሚካኤል ጉዲሳ ልጅ መሆናቸውን አንዘንጋ፡፡

አገርን እንድ የማድረጉ ሒደት ግልጽ ነበር፡፡ በዋነኝነት የመሩት አሁንም የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ልጆች ናቸው፡፡ ዛሬ ሆን ተብሎ የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ልጆች ያንን ታሪክ እንደ ልዩ የታሪክ ቁስል እንድቆጥሩ የተደረገብት ዋነኛ ምክነያት ያ ሂደት አሳፋሪ ሆኖ ሳይሆን ይህን ሕዝብ ራሱ የገነባትን ኢትዮጵያን እንዲጠላ በማድረግ እንደልባቸው በአገሪቱ ውስጥ ሊፈነጩ የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር ባሰቡ አደገኛ ሴረኞች እንሆነ ብዙ ሰው አሁንም አልገባውም፡፡  በዚህ ጉዳይ ሴረኞቹ እንደጠበቁት ተሳክቶላቸዋል፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ልጆች ከታሪክ ባለቤትናቱ አልፎም ከኢትዮጵያዊነቱ ለይተውታል፡፡ ይህ ባይሆን አንድም ኃይል አለኝ የሚል አካል ያለዚህ ሕዝብ ይሁንታ እንኳን ዛሬ ሕዝቡ በሚኖርበት ኦሮምያ በሚባለው ክልል በሌሎችም ክልል እንደልብ መዘወር ባልቻለ ነብር፡፡ በኦሮምኛ ተናጋሪው ላይ የወጠኑት እቅድ ሙሉበሙሉ የተሳካላቸው ሲሆን ዛሬ ሌላውም ኢትዮጵያነቱን እንዲዘነጋና በቀበሌ እንዲያስብ በማድረግ አንድነቱን በመበታተን ሴረኞቹ ለራሳቸው አመቻችተውታል፡፡ ብዙ ሰው ጎሰኝነትን እጠላለሁ ይላል፡፡ ውስጡ ግን እጅግ ዘረኝነት ይነበባል፡፡ ጎጃሜው አማራ እንጂ ኢትየጵያዊነት ሁለተኛው ነው፣ ትግራዩም ትግሬ እንጂ እንደዚያው፣ ሌላውም እንደዚያው፡፡ እና ማን ነው በኢትየጵያነት ሁሉንም በአንድ አይቶ ሊመራ የሚችል; ዛሬ የሆነ ቦታ ሕዝብ ሲቸገር፣ ሲገደል፣ ሌላም ሲሆን ኢትየጵያዊ ተብሎ ማሰብ ቀርቷል፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ ምናምነ ነው እንጂ፡፡ አንዳንዶች እንደውም ከሃይማኖትም ጋር አዳቅለውት ክርስቲያን አማሮች ምናምን ማለት የተለመደ ነው፡፡  ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል ልጆቻችን ሲገደሉ ለብዙዎች የሞቱት ኦሮሞዎች ናቸው እንጂ ኢትየጰያውያን አይደሉም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍም ወጭዎቹ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ምናምን በሚል እንጂ በጋራ አጀንዳ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አሁን ለብዙ ልጆቻችን መሞት ምክነያት የሆነው አመጽ ሥሕተት እንደነበር ልናገር እወዳለሁ፡፡ ጥያቄው የኦሮሞ መሬት በሚል እንጂ የፍትሐዊነት አልነበረም፡፡ ጉዳዩን አንዳንዶች እንዳሉት የማንነት ጉዳይም አይደለም፡፡ ይህ ፕላን አንዱን ገፍቶ ለሌላው መሬት መስጠ ከሆነ የፍትሀዊነት ጉዳይ ነው፡፡ የፍትሐዊነት ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ኦሮሞ ለተባለው ሕዝብ ልጆች ብቻ ሳየሆን ሁሉም በአንድነት ሊጠየቀው የሚገባ ጉዳይ በሆነ ጥያቄውም ጉልበት ባገኘ፡፡ ደግሞም ልማት በሚመስል ብዙም ጊዜ እንዳየንው ሆን ተብሎ የሆኑ ቡድኖችን ለመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡  ግን ኦሮሞ ለተባለው ሕዝብ የተለየ ባልሆነ ነበር፡፡ እንዲህ አንዱን የሚሰማው ሌላውን ደንታ የማይሰጠው የሕዝብ ጉዳት ብዙ ዓመት የተገነባ ዘረኝነት ውጤት እንደሆነ እናገራለሁ፡፡ ዛሬ የዩኒቨረሲቲ ተማሪዎች አመጸ ተነሳ ከተባለ የዘር ግጭት እንጂ የሕዝብ ጥያቄ ወይም በጋራ የተማሪዎች ጥያቄ አይደለም፡፡

አኖሌና ጨለንቆ ለምን በምኒሊክ ታሪክ ውስጥ ጎልተው እንዲታዩ ተፈለገ; እነዚህ ጦርነቶች የግድ ስለሆነ እንጂ ምኒሊክ ሆን ብለው ያደረጓቸው እንዳልሆን ግልጽ ነው፡፡ እውነት ነው አንድ ሕዝብ ሌላ አካል መጥቶ ሲወረው ራሱን መከላከል ጦርነት መግጠም ትክክለኛ ነው፡፡ ጦርነት ደግሞ ሁሌም ጉዳት አለው፡፡ ግን ጦርነት በታሪክ ሂደት ተከስቶ በሌላ ጊዜ እንደታሪክነቱ ቢዘከርም የሚነሳ ትውልድ  ያንን ታሪክ እያሰበ በቀል የሚያስብበት መሆን ባልተገባው፡፡ በአለም ላይ ያሉ አገራት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ዛሬ ባላቸው ስፋት ያሉት በጦርነት ነው፡፡ አኖሌ ዛሬ ይህ ትውልድ እንደሚነገረው ሐርካ ሙራና ሐርማ ሙራ ተከስቶበት ከሆነ በግፈኝቱ ሊወሳ ይችላል፡፡ ተከስቶም ከሆነ ትውልዱን እንደዚያ ያሉ ክስተቶች በሌላ ታሪክ እንዳይደገም ሌላ በጎ አመለካከት እንዲኖረው ማነጽ ሲገባ ቂመኛና በቀለኛ እንዲሆን ማድረግ ባልተገባ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው አዲሱ ትውልድ ሊያውም ደግሞ ታሪኩ ይመለከተዋል የተባለው የአኖሌ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላ የኦሮምኛ ተናጋሪው ባልተረጋገጠው የአኖሌ ታሪክ ተበክሏል፡፡ ይህንኑ ትውልድን በቂመኝነት መበከል ለማጠናከር መታሰቢያ በሚል በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ከመቶ ምናምን ዓመት በኋላ ሐውልት ቆሞለታል፡፡ ታሪኩ ሆኖ በትክክልም ቢረጋገጥ እንኳን ይህ ትውልድ አሁን ተሰራ በሚባለው ጥላቻን የሚያጸና ሐውልት ባልተደለለም ነበር፡፡ ይልቁን በመታሰቢየነትም ቢሆን ለሕዝቡ የሚጠቅም ት/ቤት ወይም ሆስፒታል ማሰብን በተቻለ ነበር፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት ተደረገ ስለተባለ ታሪክ ይህ ትውልድ ቂመኛ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ራሱን ግን ነጻ ማድረግ እንዳይችል አምክነውታል፡፡ ያስ ኋላ ቀር በነበረበት ዘመን ነው፡፡ ዛሬም ግን ለምን ከዚያ ባልተናነሰ ግፍ ይገደላል፡፡ አኖሌ የተባለው ግፍም ዛሬም ድረስ ሊሆኑ ከሚችሉ የጦርነት ግፎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ግን በምኒሊክ ዕውቅና ሊሆን እንደማይችል ከምኒሊክ ባሕሪ አንጻር እረዳለሁ፡፡ ይልቁንም በጦርነቱ የአርሲ ሕዝብ እንደ ተጎዳ ያዩት ምንሊክ በጣም ስለ ሕዝቡ በማዘናቸው ወታደቶቻቸውን ከድል በኋላ መሬቱን እንዳየቀማው አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ ይህ እውነት ነው! ዛሬ ኦሮሞ ነኝ እያለ ወገኑን ለሞት ከሚማግደው በላይ ምኒሊክ ኦሮሞም በሉት ሌላ ሕዝብ አሳቢው ናቸው፡፡ እውነቱ ይሄ ነው! እና ዛሬ ከመቶ ምናምን አመት ነኋላ ይህ ሕዝብ ግፍ ቀረለት; ለዚህም ምኒሊክ ተጠያቂ ናቸው;

ጨለንቆ በምን ሒሳብ እንደ ታሪክ ቁስል እንደሚነሳ አይገባኝም፡፡ ልብ በሉ ጨለንቆ ላይ የተዋጉት አቡበከር ዋሬ እንደ ጀግና መታሰባቸው ባልከፋ፡፡ ይህን ምኒሊክ ራሳቸው ዛሬ ቢኖሩ በዚህ ቅር እንማይሰኙ እገምታለሁ፡፡ የሚኒሊክ ጦርነቶች የአላማ እንጂ ማንንም በጠላትነት የማየት አልነበረም፡፡ ምን አልባትም ዋሬ በጦርነቱ ባይሞቱ እንደ ወላይታው ጦና ድል ከተነሱ በኋላ የጨለንቆ መሪ ሆነው ይቀጥሉ እንደነበር እገምታለሁ፡፡ የምኒሊክ ዓማና ራዕይ ግልጽና ምንም ሸፍጥ ያለበት አልነበረም፡፡

ሌላው በስፋት በዘመንኛ አቀንቀኞች የሚነሳው ከምኒሊክ በፊት የኦሮሞ ሕዝብ የራሱ ታሪክ፣ አስተዳደር፣ ባሕል የነበረውና ምኒሊክ ሁሉን እንዳጠፉበት ነው፡፡ ከሜዳ ተነስቶ ታሪክ አይወራም፡፡ ችግሩ የኦሮምኛ ተናጋሪውን ሕዝብ ውስብስብ አሰፋፈርና ማሕበራዊ እውነታዎች በመካድና ሁሉንም ከመዳ ወላቡ ለመቀዳት ዝም ብሎ ኦሮሞ በሚል በአንድ ጎራ መድቦ ለራስ የሚመችን ሕዝብ ለመፈጠር ስለታሰበ ነው፡፡ እንግዲህ በምኒሊክ ጠፋ ከተባለው የዚህ ሕዝብ እሴት አንዱ የገዳ ሥርዓት ነው፡፡ በምኒሊክ ጊዜ ጨለንቆዎች በገዳ ሥርዓት መምራታቸው እጠራጠራለሁ፡፡ ይሕ ሕዝብ በዚያን ወቅት አሁንም የእስልምናን እምነት የሚከተል ሲሆን ብዙ ጊዜም ከአረቦች፣ ቱርኮችና ሌሎች ሙስሊም አገራታ ባለው ግንኙነት የአስተዳደር ዘይቤው የነዚሑንው አገራት የተከተለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አርሲ የገዳ ሥርዓት ተከታይ ለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ የነበረው የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ተከታይ  እዳልነበረ አውቃለሁ፡፡ የልቁንም የገዳ ሥርዓት ለምኒሊክ ቅርብ በሁኑት የሸዋ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ዛሬም ድረስ  የካሄዳል፡፡ የገዳ ልዩ ሥርዓት ዛሬ ድረስ በቦረና ሕዝብ ይካሄዳል፡፡ ይህ ባሕላዊ ሥርዓት ለዘመናዊው አስተዳደር ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጾ ብናውቅም እንደነበረ ግን ሊቀጥል እንደማይችልም ይታወቃል፡፡

ለምን ምኒሊክ ላይ ኢላማ ተደረገ ሲባል ማንም መልስ ባይኖረውም ሆን ተብሎ ሕዝቡን ከኢትዮጵያዊነቱ ለመነጠል የምኒሊክን ታሪክ ከትውልድ አእምሮ ውስጥ ማውጣትና በጥላቻ እንዲያየው ማድረግ ሁነኛ ብለሀት እንደሆነ ታስቦበት ነው፡፡ በምንም መስፈርት የምኒሊክን ታሪክ ጠንቅቆ የተረዳ ትውልድ አሁን ላሉት ዘረኞች እሽ ብሎ የሚገዛ አይሆንም፡፡ እውነታው በምኒሊክ ጊዜ ኦሮምያም በሉት ሌላ ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር በአካባቢው መሪዎች ነበር የሚተዳደረው፡፡ ጅማ በአባ ጅፋር፣ ወለጋ በቦረዳ፣ ሌሎችም እንዲሁ፡፡ ይልቁንም ይህ ሥርዓት በሌሎች እንዲተካ ያደረገው የአጼ ኃ/ሥላሴ መንግስት ነው፡፡ ለሴረኞቹ ግን የአጼ ኃ/ስላሴ ነገር ብዙም አያሳስባቸው፡፡  በተቃራኒው ሴረኞቹ የኦሮሞም በሉት፣ ሱማሌ ወይም ሌላ ሕዝብ ከምኒሊክ ጋር የጠበቀ ታሪክ ስላለው በዚህ ሁኔታ እድል ስለማይኖራቸው ሕዝቡን የራሱ ከሆነው ከምኒሊክ ታሪክ መለየት ነበረባቸው፡፡ ታሪኩንም አማራ ለሚባለው ሕዝብ ሰጡት፡፡ ይህ የዘመናዊው ታሪክ ቅሚያ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ሆን ተብሎ በተሴረ ትውልዱን ከራሱ ታሪክ ማጣላትና የማንነት መሠረቱን ዜግነቱን በማላላት የጎጥ አመለካከት ኖሮት ከቀበሌው እነዳይወጣ በማድረግ እነሱ እነድልባቸው እየፈነጩበት ባሉ ወገኖች እንደሚዘወር አሁንም አልገባንም፡፡

ከሁሉም የኢትዮጵያ ታሪክ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ተወላጅ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው በምኒሊክ ዘመን እንደሆነ ለብዙው የዛሬው ትውልድ አይገባውም፡፡ ከላይ በታላቁዊውና ታሪካዊው አደዋ ከጠቀስኳቸው በተጨማሪ በየቦታው አስተዳዳሪ የሆኑትን ሳይጨምር የምኒሊክን መንግስት በበላይነት የመሩት የዚሁ ሕዝብ ልጆች ነበሩ፡፡ የሚኒሊክ አጎት የተባሉት የኃ/ስላሴ አባት ከላይ የጠቀስኳቸው ራስ መኮንን ወልደ መስቀል ጉዲሳ፣ ሀብተጊዎረጊስ ቢነግዴ (አባ መላ)፣ ራሳቸው ጣይቱ ብጡል በምንሊክ መንግስት ከፍተኛውን ቦታ ከያዙትና አገሪቷን የመሯት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሁሉ ግን የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ብዙ በደል ነበረበት፡፡ የምኒሊክ ሥርዓት ግን በተቃራኒው ይህንን በደል የተዋጋ ነበር፡፡ ችግሩ በቤተክርስቲያን ተስግስገው ካሉ ጠንቋይ ደብተራዎች እና ሌሎች በፊትም ያሉ ከምኒሊክም በኋላ እንደልባቸው በሁኑ አደገኛ ቡድኖች ይህ ሕዝብ እንደተበደለ አያውቅም፡፡ ይልቁንም የራሱ የሆነውን ምኒሊክኒና ታሪኩን እነዲጥል ተደርጓል፡፡ ኢያሱ በምኒሊክ ለንግስና ሲመረጥ ምኒሊክ አስበውት የነበረው አሳቸው የጀመሩትን የኦሮምኛ ተናጋሪውም ሆነ ሌላውን ሕዝብ በፍትሐዊነት ያገለግላል ብለው ነበር፡፡ ኢያሱም የቱንም ያህል ወጣት ቢሆኑም አያታቸው ምንሊክ የመከሯቸውን ነበር የጀመሩት፡፡ ኢያሱም ግን በአደገኛ ደብተራዎችና ሴረኞቹ ወደቁ፡፡ ይህ ትውልድ ከዚህ እወነት ተጋረዷል፡፡ ጠላቶቹ የነገሩትን እየሰማ ራሱን አጥቷል ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህ እኔ ያወቅኩት እውነት ነው፡፡ የሄ እውነት አይደለም የሚል ቢኖር ልታረም ፍቃደኛ ነኝ፡፡ አመሰግናለሁ!!

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Blog Stats

  • 52,481 hits
Advertisements
%d bloggers like this: