Uncategorized

ጽፌው ከወጣልኝ! BefeQadu Z. Hailu

 

እኔና @BlenaSahilu በፍትሕ ሚኒስትር ደጃፍ የሞቀ ወሬ ይዘን እየሄድን ነበር። ፀሐይዋ ግንባር-ግንባራችንን እያለችን ስታስጨንቀን ድንገት አቅጣጫ ቀየርን። ወዲያው ግን ከጨዋታችን የሚያናጥብ ድምፅ ሰምተን ዞር ስንል የፍትሕ ሚኒስትሩ አጥር ላይ ክላሹን ጭኑ ላይ ካስቀመጠ የፌዴራል ፖሊስ ጋር ተገጣጠምን። ያልጠበቅነው ጥያቄ ተከተለ፤ «ምን ፈልጋችሁ ነው በዚህጋ የምትመላለሱት?» ብሌን በትህትና መለሰች «አይ ለፀሐይዋ ጀርባችን ለመስጠት ነው»። ፖሊሱ ወይ መልሳችን አልተዋጠለትም ወይም ሥልጣኑን ማሳየት አምሮታል።

ለማስረዳት ሞከርን። «ያለንበት እኮ መንገድ ነው። መመላለስ መብታችን ነው» አልነው። እሱ ግን ልናስረዳው በሞከርን ቁጥር ቁጣው እየተባባሰ መጣ። ብዙ ተመላለስን። ብሌንም፣ እኔም ልናስረዳው ብዙ ደከምን። እሱ ግን መልሶ መላልሶ እዚያው ነው።

«ምን ፈልጋችሁ ነው እዚህጋ የምትቆሙት?»

«ኧረ እኛ አልቆምንም በዚህጋ እያለፍን ነው። ተቋሙን ቀና ብለንም አላየነውም። ደግሞስ ብንቆምስ?! የሕዝብ መንገድ አይደል እንዴ የሚከለክለን ሕግ አለ?» አልኩኝ።

ምናልባት የተናገርኩት አልገባውም። ፖሊሱ የደቡብ ሰው እንደሆነ አነጋገር ዘዬው ያስታውቃል፤ አማርኛ ይከብደዋል። ምናልባትም ይገ’ባኛል ብሎ የሚያስበውን ያክል ክብር አልሰጠሁትም ይሆናል። ምናልባት ወይም ሴት ባለመሆኔ እና ደቃቃ በመሆኔ ለመምታት አጓጉቼው ይሆናል።

«ብቆምስ ትላለህ? ቁም እስኪ!…» እያለ በቁጣ ዛተ። ነገሩ መሥመር እንዳለፈ ገባኝ። ግቢ ውስጥ አስገብተው ቢደበድቡንስ የማን ያለህ ይባላል? በጥይት ቢጠብሱንና “የደኅንነት” ሰበብ ቢሰጡስ ማን ይጠይቃቸዋል? ፍርሐቴ መጣ። «ብሌን፣ እንሂድ በቃ» አልኳት እና መንቀሳቀስ ስንጀምር። ከአጥሩ ላይ ዘሎ ወረደ። «ና!… ና!…» እያለ እያምባረቀ ይከተለን ጀመር። «በሕግ!…» እያልኩ ሸሸሁ። ብሌን «በፍፁም አትወስደውም…» ብላ መሐላችን ገባች። አንድ ሞተረኛ መንገደኛ ጭቅጭቃችንን አይቶ ቆመ። ከወዲያኛው በር ሌላ ፌዴራል ፖሊስ መጣ። ሞተረኛው ሊንቀሳቀስ ሲል ብሌን «በናትህ አትሂድ አለችው…» ቆመ። ሌላም ባለመኪና ጭቅጭቃችንን አይቶ መኪናውን አቆመ እና አንገቱን ዝቅ አድርጎ ማየት ጀመረ።

ሌላኛው ፌዴራል ፖሊስ በተሻለ ስክነት ምን እንደተፈጠረ ለመጠየቅ እና ለማዳመጥ ሞከረ። እሱም የደቡብ ሰው እንደሆነ ንግግሩ ያስታውቃል። እኛም የራሳችንን ስንናገር፣ ፖሊሱም «እዚጋ እቆማለሁ ብሎ ነው» አለ። ብሌን «አትዋሽ፣ አትዋሽ እንደሱ አላለህም…» በሚል በከፍተኛ ብስጭት መለሰችለት። በተነጋገርን ቁጥር እልኋ ገንፍሎ እምባ፣ በእምባ ሆነች። ያንኛው ፖሊስ ነገሩን ለማረጋጋት ጣረ። መኪናውን ያቆመው ሹፌርም ወርዶ መገላገል ጀመረ። ብሌን እልኋ ከፖሊሱጋ ለመደባደብ እስከመፈለግ አድርሷት ነበር። በገላጋዮቹ መምጣት፣ ኋላ በመጣው ፖሊስ ገ’ራምት፣ እና በብሌን እምባም ከመጣብን መዓት ተረፍን።

ከዚያ በኋላ በስሜት መጎዳት ተውጠን የተነጋገርናቸው ቃላት ጥቂት ናቸው። «አሁን እሺ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው?» ተባባልን። ብሌን «አንድ ነገር ቢያደርጉን ማንም እንደማይጠይቃቸው ያውቃሉ። ሲስተሙ ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ምንስ ቢያደርጉን ማን ይጠይቃቸዋል?» አለች። ጭንቅላቴን ከመወዝወዝ በላይ መልስ አልነበረኝም።

ግን፣ ግን አሜሪካ ብሄድና እንደሁለተኛ ዜጋ በዋይት ሀውስ ደጃፍ ባልፍ «ለምንድን ነው በዚህ’ጋ የምታልፈው?» እባል ይሆን? ወይ ሀገር!

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Blog Stats

  • 52,293 hits
Advertisements
%d bloggers like this: