Uncategorized

ፔፕሲ ኮላ የተቀማ የሰው ንብረት – አገሬ አዲስ

ሰሞኑን በድረገጽ ላይ ሰፍሮ ያነበብነውና በራዲዮ ስርጭትም ያዳመጥነው ጉዳይ የፔፕሲ ኮላ “ባለቤት”የሆነው ቱጃሩ ሸህ ሙሃመድ አላሙዲን ከወያኔ ባለስልጣኖች ጋር በማበር የሚያደርገውን ምዝበራ በመቃወም በኢትዮጵያ ውስጥ ፔፕሲ ኮላን ሕዝብ ገዝቶ  እንዳይጠጣ የተአቅቦ(ቦይኮት) ጥሪ በመሰራጨት ላይ መሆኑን ነው።

ይኸው ቱጃር ከባለስልጣኖች ጋር በመመሳጠር አያሌ የአገሪቱን ዋና ዋና የንግድ ተቋማት እንደ አዶላ የወርቅ ማዕድን የመሳሰሉትን  ጭምር ከመቆጣጠሩም በላይ ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችን በሙስና ወስዶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማይቀርብና የማይተርፍ ምርት እየሰበሰበ ወደ አባት አገሩ ሳውዲ አረቢያ በመላክ ለአረቦች የምግብ አቅርቦት እያሟላ ገንዘቡም በዛው በውጭ አገር ባንክ እንዲከማች የሚያደርግ ዘራፊ ነው።በጣም የሚገርመው ነገር በይፋ ከውጭ አገር ገንዘቡን ይዞ የመጣ ኢንቬስተር እየተባለ ሲነገር በገሃድ የሚታየው ግን አብዛኛው ገንዘብ ከኢትዮጵያ ባንክ በነጻ ወይም በትንሽ ወለድ የሚወስደውና የሚጠቀምበት መሆኑ ነው።ባገራችን አባባል”አንድ ጭብጥ ይዞ ወደ ክምር ጠጋ”የሚለው አባባል በሚገባ ይገልጸዋል።ስለሰውየውና ስለባለስልጣኖቹ የጥቅም ትስስር ይጻፍ ቢባል ወንጀል የሚሰራበት አገር የኢትዮጵያ መሬት ወረቀት ቢሆን አይበቃውም።

Boycott p

ይህን ደባ ለመስራት ከባለስልጣኖቹ ጋር በመተባበር ከሚጠቀምበት በተጨማሪ አንዱ አሳሳች ስልት በአገሪቱ አሉ የተባሉትን ታዋቂ ግለሰቦችን በተለይም በኪነት መድረክ ላይ የሚታወቁትን በጥቅም ሰንሰለት በማሰር፣በመሸለምና ስጦታ በመስጠት የማስታወቂያ ሰሌዳ አድርጎ በመጠቀም ደግና ለጋሽ መስሎ በመታየት ነው።ሌላው  በገንዘቡ ተማምኖ በሴቶች ላይ የሚጫወተውና መረን በለቀቀ ግንኙነት የሚፈጽመው ወራዳ ተግባር የሚዘገንን ሲሆን የብዙዎቹን ለግላጋ ወጣቶች ቀልብ የሳበና ያሳሳተ አደገኛ ምሳሌ የሆነ ነው።በአዲስ አበባ ከተማ ያሰራው ትልቁ የሸራተን ሆቴል ለአገሪቱ የቱሪስት ስበት ይጠቅማል ቢባልም የአገሪቱ ባለስልጣናትና ቤተሰቦች በነጻ የሚስተናገዱበት ክለብ በመሆን ያገለግላል፣ከክበብም በላይ ከውጭ አገር የገቡና በአገሪቱ የበቀሉ መዥገሮች የዘረፋ እቅድና ዝግጅት የሚነድፉበት፣ የጸጥታና የመከላከያ ሃይሉ ባለስልጣኖች በሕዝቡ ላይ የሚሰነዝሩት ቅጣትና የበቀል እርምጃዎች በአልኮል ግፊት የሚቀርጹበት የተንኮል ዋሻ ሆኗል።

ከሁሉም ዘረፋዎች ቀዳሚነቱን ቦታ የያዘው የፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ ነው።

ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ስለፔፕሲ ኮላ አመሰራረት ትንሽ ልበል፤

ፋብሪካው የተቋቋመው እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1958ዓ.ም.ነው።መርቀው የከፈቱትም አጼ ሃይለ ሥላሴ ናቸው።በጊዜው ዓለም አቀፍ የንግድ እውቅና ከነበራቸው ዘርፎች በተለይም በኢትዮጵያዊ ንብረትነት ከሚንቀሳቀሱት አንዱና ትልቁ በመሆኑ የፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ ከኮካ ኮላ ቀጥሎ ትልቅ ስርጭት የነበረው የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ነበር።

መስራቹና ባለቤቱ ፣በሐረር ከተማ በመጋቢት 16ቀን 1912 ዓ.ም.የተወለዱት አቶ ጌታቸው ገ/ዩሃንስ ናቸው። አቶ ጌታቸው ባላቸው ጥረት አስተዋይና ፈጣን አእምሮ የድህነትን ማነቆ ለማለፍ የቻሉና በወቅቱ ለብዙ ታታሪ ኢትዮጵያውያን እንደምሳሌ የሚጠቀሱ ነበሩ።በልጅነታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በዃላ የፈረንሳይ ቋንቋና ትምህርት ለመከታተል ወደ ድሬዳዋ አመሩ። ወደ ድሬዳዋ ሲሄዱ የመጓጓዣ እጥረት በመኖሩ በእግራቸው ለቀናት ተጉዘው ነበር የደረሱት።እዛም ዘመድ ጋር በመጠጋት የፈረንሳይ ትምህርታቸውን ተከታተሉ።ጣሊያን አገራችንን ወሮ በነበረበት ወቅት የጣሊያንን ቋንቋ ለማወቅ አስቻላቸው።ጣሊያን ከወጣ በዃላ በአገራችን መረጋጋት ሲጀምር ወጣቱ ጌታቸው አነስተኛ የዳቦ መጋገሪያ ቤት በድሬዳዋ አቋቋሙ።ጎን ለጎንም የፈረንሳይ ቋንቋ በማወቃቸው ፈረንሳዮች ባቋቋሙትና በሚያስተዳድሩት የባቡር መስመር አገልግሎት መስሪያ ቤት በቲኬት ቆራጭነት ተቀጥረው ለዓመታት ሰሩ።እንዲህ ቀስ በቀስ እያሉ የሚያገኙትን ገንዘብ በብልሃት በመያዝ አትራፊ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዋል  የሚኖሩበትንና የሚያከራዩትን ቤት ለመስራት በቁ።ከዛ በመቀጠል በድሬዳዋ የነዳጅ ማደያ ባለቤት ለመሆን በመቻላቸው ገቢያቸው እያደገ መጣ፤በአዲስ አበባ ቤቶችን ከመስራት  አልፈው በአዋሽ አካባቢ በሰብል ወቅት እስከ ሁለት ሽህ ወቅታዊ ሰራተኛ የሚተዳደርበትን፣ተባይ በአውሮፕላን የሚረጭበትንና ፈረንጆች በአማካሪነትና በሙያ የሚያገለግሉበትን ትልቅ እርሻ ጀመሩ። የአዲስ አበባ ባንክም ስራውን ሲጀምር ካቋቋሙትና የብዙ ድርሻ ባለቤቶች(Share holders)መካከል አንዱ ነበሩ። በዛም አልቆመም የአንበሳ ኢንሹራንስ መስራች ከነበሩት አንዱ ነበሩ።የአቶ ጌታቸው እድገት አንዳንድ ባለስልጣኖችን አላስደሰተም ነበር።ግን ምንም ጥፋት ስላላገኙባቸው ሊያጠቋቸው አልቻሉም፤እንደውም በጋብቻ ሰንሰለት ለማሰር ፍላጎት ነበራቸው።አቶ ጌታቸው ግን የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቋሙ እንጂ የድህነት ሚስታቸውን፣የልጆቻቸውን እናት ሊለዩና በሌላ ሴት ለመለወጥ አልፈለጉም።አቶ ጌታቸው እራሳቸውን ለማሳደግና ለማስተማር አልቦዘኑም፤ከፈረንሳይና ከጣሊያንኛ ጎን ለጎን እንግሊዝኛና አረብኛ አስተካክለው የሚናገሩ ሲሆን ከአገር ውስጥም አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣አደርኛና ግዕዝ ከመናገር አልፈው የአገራችንን ታሪክና የቋንቋዎቹን ምንጭ በሚገባ የመተንተን ችሎታ ነበራቸው።

ጥረታቸው የፔፕሲ ኮላን ፋብሪካ ከማቋቋም ደረጃ ላይ አደረሳቸው።በነበራቸው ገንዘብ ላይ የባንክ ብድር ጨምረውበት  ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በመክፈት የሚተዳደሩበትን ፋብሪካ አቋቁመው በንጉሱ አስመረቁ።

ፋብሪካውን ለማሳደግና ሌላም ተጨማሪ ለስላሳ መጠጦችን ለማዘጋጀት ዕቅድ ላይ እንዳሉ የየካቲቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከተፍ አለ።የለውጡ ጎርፍ አገሪቱን ከዃላ ቀርነት አላቆ ወደተሻለ አቅጣጫ ያመራታል ሲባል ይባስ ብሎ ወደ ገደል የሚከት የወታደር አምባገነን ስርዓት ተተካና እንደ አቶ ጌታቸውና ከሊስትሮነት ተነስተው የመጠጥ ፋብሪካና የአገር አቀፍ ሰንሰለት ሆቴል ባለቤት የሆኑትን እንደ አቶ በቀለ ሞላ ያሉትን አገር በቀል ሃብታሞች በመንከባከብና በርታ  በማለት ፈንታ እያሳደደና እየነጠቀ የድህነት እኩልነትን ያረጋገጠ ስርዓት አሰፈነ።በዚህ እውር ጥላቻና ምቀኝነት በሚያሽከረክረው ስርዓት የፋብሪካ ባለቤት ብቻ ሳይሆን  የሚያከራያት አንዲት ክፍል ቤት ያለችው ሳይቀር ፣በገጠሩ እርሻ ላይ በብድር የተገዛ የእርሻ መኪና(ትራክተር) ባለቤት የሆነ ሁሉ በዝባዥና አቆርቋዥ ተባለና ወደነበረበት የድህነት ጠርዝ ተወረወረ።ያ የእድገት ጭላንጭል የሚታይበት እንቅስቃሴ ሁሉ ተንኮታኮተና ሰራተኛው  መብቱን ተነፍጎ፣በለውጡ ኑሮው ወደ ተሻለ ደረጃ ሳይቀየር የጥቂት ወታደሮች አገልጋይ ሆነ፤የተወረሰውም ንብረት የስርዓቱ የመጨቆኛ ባጀት ምንጭና ባለስልጣኑ እንደፈለጉ የሚያዙበት የግል ሃብት ሆነ።

በደርግ የታወጀው የንጠቅ አዋጅ በአቶ ጌታቸውም ላይ ደርሶ ፋብሪካው፣ሰፊ የእርሻ ቦታው፣የከተማ ቤቶቹ ሳይቀሩ ተወረሱና ለሚኖርበት ቤት ብቻ ባለቤት አደረገው።አቶ ጌታቸው የፔፕሲን ፋብሪካ ለማሳደግ ካቀዳቸው አንዱ የትራንስፖርት ዘርፉን ማሻሻል ስለነበረ ሃያ ሶስት የጭነት መኪናዎችን ለማስመጣት ቅድሚያ ክፍያ በባንክ በኩል ከፍለው በመጠባበቅ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው የውርስ አዋጅ የታወጀው። በግርግሩ መኪናውም ሳይመጣ ገንዘባቸውንም ሳያገኙ ቀሩ።በሁኔታው የተበሳጩት አቶ ጌታቸው ሁሉንም ነገር ጣጥለው ገዳም ገቡ።ቤታቸው እንዳልነበረ ሆነ፤ትዳራቸው ፈረሰ፣ቤተሰብ ተበተነ።ችግር ብቻውን አይመጣም እንደሚባለው ተደራረበባቸው ፤ግን ተመስገን ብለው በጸጋ ተቀበሉ።ከአምስት ዓመት የገዳም ኑሮ በዃላ ተመልሰው ሰራተኛቸው ትጠብቅላቸው ከነበረው ቤታቸው ገቡ።በዚህ ላይ እንዳሉ ነው የደርግ ስርዓት ተወግዶ ወያኔ የሚቆጣጠረው ስርዓት የሰፈነው።ወያኔ ሲገባ የደርግን አረመኔ ተግባር እያወገዘ፣የተሻለ ስርዓት ለማስፈንና በሕገወጥ መንገድ የተወረሱ ንብረቶችን ለባለቤቶቹ ለመመለስ ቃል ገብቶ ነበር።በደርግ ከተነጠቁት መካከል አቶ ጌታቸውም የይመለስልኛል እምነትና ጉጉት ነበራቸው።ግን የተከናወነው ሌላ ያልጠበቁት መሰሪ ተግባር ነበር።ለወያኔ ቅርበት የነበራቸው ግለሰቦች ንብረታቸው ሲመለስ ለስርኣቱ ቅርበት የሌላቸው በተለይም የአማራ ተወላጆች የሆኑት የንብረታቸው ባለቤቶች አልሆኑም።አቶ ጌታቸው በመመሪያው መሰረት ይገባኛል ቢሉም ሰሚ ጆሮ አላገኙም።

አቶ ጌታቸው ቆርቁረው የመሰረቱት የፔፕሲ ኮላ ፋብሪካ በአዲስ መጦቹ በወያኔ ባለስልጣናት ውሳኔ ለጥቅም አጋራቸው ለሸክ ሞሃመድ አላሙዲን በሽያጭ ስም ተሰጠው።ገዢው የማን ንብረት እንደነበረ ባገኘው መረጃ ከባለቤቱ ስለድርጅቱ አሰራርና ታሪክ መሰብሰብ ስለአስፈለገው አቶ ጌታቸውን አፈላልጎ በማግኘት ንብረቱን ለመግዛት ማሰቡንና ሲገዛም አቶ ጌታቸውን በሽርክና ሊመልሳቸው እንደሚፈልግ ቃል በመግባት የሚፈልገውን ዝርዝር ለመሰብሰብ ቻለ።ከጥቂት ሳምንታትም በዃላ የግዥው ሂደት ተጠናቀቀና አቶ ጌታቸውን የፔፕሲ ተቋም ግማሽ ባለቤት ለማድረግ የገባውን ቃል ጥሶ ሜድሮክ በመባል ለተሰየመው የድርጅቶች ጥምረት  በሲኒየር(በአንጋፋ)አማካሪነት ብቻ ተቀጥረው እንዲሰሩ አደረጋቸው።በዚህ ወቅት ነበር ሸክ አላሙዲን ለአቶ ጌታቸው ለፋብሪካው መግዣ ተጠይቆ የከፈለው አንድመቶ ሃያ ሚሊየን ዶላር ሆኖ ሳለ በይፋ የተገለጸውና በሰነድ ላይ የሰፈረው ግን አንድ መቶ አስራ አምስት ሚሊዮን  ዶላር ተብሎ ቀሪው አምስት ሚሊዮን ዶላር በባለስልጣኖቹ ኪስ መግባቱን ሹክ ያለው።በዚህ የሽያጭ ዝውውር የተሳተፉት ቀዳሚ ባለስልጣኖቹ ሲሆኑ አምስቷን ሚሊዮን የተቦጫጨቁት ከመለስ ዜናዊና ከታምራት ላይኔ በተጨማሪ ለሁለቱ ቅርበት ያላቸው እንደሆኑ አላሙዲን አልደበቀም።በዚህ እራሱንም እንደተበዳይ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል።

ምንም እንኳን በአገር ውስጥ እንደ ቀሪዎቹ ባለሃብቶች፣እንደ አዋሽ ሆቴል ባለቤቶች ንብረቴ ይመለስልኛል ብለው በጉጉት ይጠብቁ የነበሩት ምኞታቸው ባይሳካም በሕግና ስርዓት ባለበት አገር ቀደም ሲል ለሚያካሂዱት እንቅስቃሴ ከውጭ አገር ለሚያስገቡት ዕቃ መግዣ የሚሆን ገንዘብ ካስቀመጡበት የውጭ አገር ባንክ ያላቸውን ንብረት ለመጠየቅ ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም። እኔም የዚህ ታሪክ ጸሃፊ ባለኝ የቤተሰብነት ትስስር ጉዳዩን  እንድከታተል ሕጋዊ ውክልና ሰጥተውኝ ከተባለው ባንክ ባለስልጣኖች ጋር ተነጋግሬ ነበር።መልስ የምንሰጠውና ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ ያለብን ከባለቤቱ ጋር ነው በማለት ለእኔ ዝርዝሩን ላለመስጠት ወሰኑ።ባሳሰብኩት መሰረት የባንኩ ባለስልጣኖች ከባለቤቱ ከአቶ ጌታቸው ጋር ግንኙነት መሰረቱ።በመጨረሻው ገንዘቡን ቀደም ሲል እራስህ አውጥተሃል፣ የቀረ የለም በማለት ካዷቸው።አቶ ጌታቸውም ከ1974 ጀምሮ ከአገር እንዳልወጡ ማስረጃ ቢያቀርቡም ባንኩ ሊቀበለው አልፈለገም፤የሕግ ባለሙያዎችም እንደጠረጠሩት  ብዙ ባንኮች ለዓመታት የሚከታተል ሰው የሌላቸውን ሂሳቦችና ንብረቶች በሙት ስም እንደሚቀሙና ባለስልጣኖቹ በጥበብ እንደሚቀራመቱት ነው። በውጭ አገር ዘራፊዎችና በገዛ ወገናቸው ብዙ ንብረታቸውን ያጡት አቶ ጌታቸው የጀመሩትን ሕጋዊ ሙከራ ከግቡ ሳያደርሱና ንብረታቸውን ከእጃቸው ሳያስገቡ በተወለዱ በዘጠና ሶስት ዓመታቸው በጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።መንግስት ለሸህ አላሙዲን የሸጠውንና በውርስ ስም የወሰደባቸውን አንጡራ ሃብት ባለቤቱ በህይወት ኑረው ባይረከቡም ልጆቻቸው የማግኘት መብት አላቸው፤የሕግ የበላይነትና ሕዝባዊ ስርዓት ሲሰፍን በሕገወጥ መንገድ የተዘረፉት የሕዝብ ንብረቶች ለባለቤቶቻቸው ወይም ለወራሾቻቸው መመለሳቸው አይቀሬ ነው።እስከዚያው ድረስ ንብረቱን ለያዙት የማፊያ ቡድኖች የገቢ ምንጭ ላለመሆን ሕዝቡ አድማ ሊመታ ይገባዋል፤ፔፕሲንም ላለመጠጣት የሚደረገው ዘመቻ ተገቢና አስፈላጊ ነው።ወራሽ ልጆቻቸው በውጭ አገር ባንክም የተዘረፈባቸውን ገንዘብ እንዲሁ ጠበቃ አቁመው ቢከራከሩ የሚያጡት አይመስለኝም።

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

Blog Stats

  • 52,293 hits
Advertisements
%d bloggers like this: