Uncategorized

ባለሙያነት እና የፓለቲካ አመለካከት በሀገራችን: (አቤል ዋበላ)

ባለሙያነት እና የፓለቲካ አመለካከት ለየቅል ናቸው፡፡ በሀገራችን ግን ይህ ልዩነት ፈርሷል፡፡ መስመርህን ከገዢዎች ጋር ካላስተካከልክ በባለሙያነት ሀገርህን ማገልገል አትችልም፡፡ በእውቀት በጉልበትህ ደክመህ ራስህን እና ቤተሰብህን መመገብ የማይታሰብ ነው ፡፡ ሀሳቡን በተለያየ መልክ የሚገልጽ ወይም በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፍ ሰው የአስተሳሰብ ልዩነቱ ሀገሪቱን እንመራለን ከሚሉ ጥቂት ሰዎች ጋር ነው፡፡ ህዝቡ በምርጫ እንድንመራው መርጦናል የሚሉት እነዚህ ጥቂት ሰዎች በተረዱት መጠን የወደዱትን ያደርጋሉ፡፡ ሌላው ዜጋ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ልምድ እና ከሰው ልጆች ታሪክ በመነሳት፣ አካዳሚያዊ ዕውቀቶችን በመጠቀም ልክ የሆነውን ይበል ይላል ተሳሳተ የሚለውን ደግሞ ይተቻል፡፡ የሀገሪቱ ሕግም ይህንን ይፈቅዳል ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ ጤነኛ ሆኖ እንዲቀጥል ትችቱ የግድ እንደሆነ ያሰምርበታል፤ ሕጋዊ ከላላም ያደርጋል፡፡ የበረታው ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁሞ ከገዚዎች የተለየ (የተለየ የሚለው ይሰመርበት) መርሐ ግብር ቀርጾ ለመንግሥትነት መወዳደር ይችላል፡፡ በዚህ የስልጣኔ መንገድ ብዙዎች ቢጓዙበትም እኛ ግን ይህንን አልታደልንም፡፡
ባለጊዜዎች ከእነርሱ የተለየ አመለካከት ያለው ሰው ሲያጋጥማቸው እርሱን ለማጥቃት ሁለት እርከን ያለው አሰራር ይዘረጋሉ፡፡ የመጀመሪያው እነርሱ እራሳቸው ነፍጥ ያነገበ ሰው በመላክ በቀጥታ የሚሳተፉበት ነው፡፡ የሚላከው አንጋች ደግሞ በልቶ ማደሩ ብቻ ስለሚያሳስበው የአስተሳሰብ አድማሱም ውስን ስለሆነ ይህ ከገዢዎች በአመለካከት ብቻ የተለየውን ሰው ሕገ መንግስታዊውን ብቻ አይደለም ሰብዓዊ ክብሩን ገፎ ከሰውነት በታች ያወርደዋል፡፡ ሁለተኛው አሰራር ደግሞ መንግስት በቢሮክራሲው ውስጥ የሰገሰሰጋቸው ሆድ አደር ባለሙያዎችን ተጠቅሞ የሚከውነው ነው፡፡ እነዚህ በሁለተኛው እርከን የሚገኙ የስርዓቱ አገልጋዮች በመጀመሪያ እርከን የሚወሰዱ እርምጃዎችን ተከተለው ተጨማሪ የመብት ጥሰት ይፈጽማሉ ወይንም በመጀመሪያ እርከን የተወሰደ እርምጃ ባይኖር፣ ትዕዛዝም ባይተላለፍላቸውም አለቆቻቸው የማይወዱትን ጠንቀቀው ስለሚያውቁ የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ ይህ የፖለቲካ ታማኝነታቸውም ከሌሎች ከእነርሱ ከተሻሉ ብርቱ ባለሙያዎች አስመርጦ በወንበር ላይ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡ የዐሳብ ልዩነትን የማፈኑ ሰንሰለት በዚህ አያበቃም፡፡ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ያሉ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የግል ድርጅቶችም ህልውና የተመሠረተው የሀገሪቱን ሕጎች በማክበር ሳይሆን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የወደዱትን በመውደድ የጠሉትን በመጥላት ነው፡፡
በዚህ የግፍ ሰንሰለት ከተንከባለሉ ጓደኞቼ አንዷ ኤዶም ካሳዬ ናት፡፡ ኤዶምካን የማውቃት በሶሻል ሚዲያ ነው፡፡ በጊዜው በዞን ዘጠኝ የምናረጋቸውን እንቅስቃሴዎች በቅርበት ከሚከታተሉና ወዳጃዊ ሒስ ከሚሰጡን ለጋስ ባለሙያዎች እንዷ ነበረች፡፡ በወቅቱ ኤዶምካ በስራ ምክንያት ውጭ ሀገር ነበረች፡፡ ከመሄዷ በፊት ከጦማሪ ጓደኞቼ ጥቂቱን ማወቋን ስረዳ ወደ ሀገር ቤት መጥታ በአካል እስክንተዋወቅ መጓጓት ጀመርኩኝ፡፡ ከዓመት በላይ የፈጀ ስራውን ጨርሳ ስትመለስ ተዋወቅን፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ የራሷ የሆነ አመለካከት ያላት፣ ሰው ማስቀየም የማትፈልግ፣ ሳቅ ጨዋታ የምትወድ አሪፍ ልጅ ሆና አገኘኋት፡፡ ስለ እስክንድር ነጋ አውርታ አትጠግብም ነበር፡፡ እስክንድርን መውደዷ እና የፒያሳ ሳንቡሳ ከእኔ ጋር አርቦሽ አደረገን፡፡
ማዕከላዊ እንደገባው በሀገር ውስጥ የሚገኙ የዞን ዘጠኝ ጓደኞቼን እንደማገኝ አልተጠራጠርኩም ነበር፡፡ ኤዶምካን ሳያት ግን በልቤ ከባድ ሀዘን አለፈ፡፡ ወዳጅ በችግር ጊዜ ከጎን ሆኖ አይዞን ይላል ኤዱ ግን መዋረዱንም፣ መሰደቡንም፣ ቶርቸሩንም፣ ፍትህን አለቦታው መፈለጉንም አብራን ተካፈለች፡፡ በሚሞቀው ፈገግታዋ መንፈሳችን እንዳይዝል አበረታችን፡፡ ከዜግነታችን በቀር ሌላ በደል እንደሌለብን ለኛም ለሌላውም ሰው ምስክር ሆነች፡፡ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው የተሳከረ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባሰገኘው ውጤት የፕሬዘዳንት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ተከትሎ ከወህኒ ቤት ተለቀቀች፡፡ ከወህኒ ብትወጣም እስረኝነቷ አላበቃም፡፡ ስሟ ከሀገር መውጣት ከማይችሉ ሰዎች መዝርዝር ውስጥ ስለሆነ በአሜሪካን ሀገር ያገኘችው የትምህርት ዕድል መጠቀም አልቻለችም፡፡ የኢትዮጵያ ኢምግሬሽን ባለስልጣን ሀገሪቱን እንመራለን ከሚሉ ጥቂት ሰዎች የተለየ አመለካከት ብቻ ስላላት የእንዲትን ዜጋ ፓስፖርት ነጥቆ የዜግነት ሰነድ አልባ አድርጓታል፡፡
ከመታሰሯ በፊት በፕላን ኢንተርናሽናል በኮኦርዲኔተርነት ትሠራ ነበር፡፡ ከእስር እንደተፈታች ወደስራ ገበታዋ ለመመለስ ብታመለክትም ድርጅቱ ሊቀበላት አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም እሷን ቀጥሮ ማሰራት በመንግስት አይወደድም ስለዚህ መንግስትን ከማስከፋት ምንም በደል የሌላባትን ሠራተኛውን መጉዳት ፈለገ፡፡ ከላይ ትዕዛዝ ተላልፎ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ያለ ትዕዛዝ መስመርን ማስተካከል አካሄድን አንድ ማድረግ የዘመኑ መንፈስ ሆኗል፡፡ ይህ ነው መሰበር ያለበት፡፡ በዚህ በቀጠታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚወሰድ ሕገ ወጥ እርምጃ ከስራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ እንኳን እንደኛ ያለ ተራ ዜጋ አይደለም ስመጥሮቹ ምሁራን ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋም ከዚህ ፍርደገምድልነት አላመለጡም፡፡ የቅርቡን ላንሳ ብዬ እንጂ ከስርዓቱ ጋር በዐሳብ ስለተለያዩ ብቻ ዋጋ የከፈሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ስርዓቱ ዕድሜውን ከሚያራዝምበት ስልቶች አንዱ ይሄ የዐሳብ ልዩነትን መጨፍለቅ ነው፡፡ይህም በርካታ ዜጎችን ከፖለቲካዊ ተሳትፎ እና የመብት ጥያቄን ከማንሳት ተገደብው ይገኛሉ፡፡ ከብዙዎች ጋር እንተዋወቃለን ሰላማዊ ሰልፍ ብሳተፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ብሆን፣ ሀሳቤን በሚዲያ ብገልጽ ከስራዬ ተባርሬ የምበላው አጣለው በሚል ስጋት ነው ሁሉም የሆዱን በሆዱ ይዞ ዝም ያለው፡፡
ኤዶም በሕግ ወጥ መንገድ የሥራ ውሏ መቋረጡን ተቃውማ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ቄራ ምድብ ችሎት ክስ መስርታለች፡፡ ፍርድ ቤቱ ነገ ሐሙስ ከጠዋቱ 3፡00 ክርክሩን ያዳምጣል፡፡ የዐሳብ ብዛኅነት መከበር የሚሳሰበን ሁላ በችሎት ተገኝተን ልንታዘብ ይገባል፡፡ነገ ወደ ቄራ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እሄዳለው፡፡ የምሄደው የትላንት ዝምታዬ እየቆጨኝ ነው፡፡ የምሄደው ዛሬ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በማህሌት ፋንታሁን ላይ፣ አምቦ ዩንቨርሲቲ በዘላለም ክብረት ላይ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእኔ ላይ የሚያደርሱብንን በደል ተቃውሜ ነው፡፡ የምሄደው ‘የነገዋ ኢትዮጵያ’ ሰዎች በፓለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ከስራ ገበታቸው የማይፈናቀሉባት፣ ባለሙያና ባለሙያነት የሚከበሩባት፣ የሰራተኛ እና የሙያ ማህበራት ለሠራተኛው መብት እና ሙያዊ ክህሎት የሚተጉባት እንድትሆን ካልሆነችም ደግሞ እንደምትፈርስ ትንቢት ወይም እንድትፈርስ ብይን ለመስጠት ነው፡፡
የዐሳብ ብዛኀነት ይለምልም!

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

facebook

https://www.facebook.com/

Blog Stats

  • 54,675 hits
Advertisements
%d bloggers like this: