Uncategorized

እኔና ሀያሲዎቼ! Bewketu Seyoum

(ቁጥር 1)
ከአሜን ባሻገር በተባለው መጽሐፌ በላስታ የሚገኙትን የሮሀን ውቅር መቅደሶች ጎብኝቼ የተሰማኝን አድናቆት ጽፌ ነበር፡፡ መጣጥፌን የጀመርኩት እንዲህ በማለት ነው፤
” የላሊበላ ኣዳራሾችን በቃላት ወይም በፊልም ለማስረዳት መሞከር አሪፍ ቅኔን በዱዳ ቋንቋ ለማስረዳት እንደመሞከር ነው፡፡ የላሊበላን አዳራሾች ምን ብለን እንጥራቸው?ካንድ ዐለት የተፈለፈሉ መቅደሶች የሚለው አገላለጽ ያንስባቸዋል፡፡“
ይህ የአድናቆት አገላለጽ እንደ ነውር ተቆጥሮ ያነቅፈኛል ብየ እንዴት ልገምት ፡፡ አንዳንድ ወንድሞቼና እህቶቼ ከተጠቀሰው አንቀጽ ማህል “ አዳራሽ ” የምትለውን ቃል ነጥቀው ተነሡብኝ፡፡ ይልቁንም አንዲት ለክብራቸው ስል ስማቸውን የማልጠቅሰው -፤ እሣት ጎርሰው ፤እሣት ለብሰው፤ ጸጉራቸውን ተተኩሰው፤ የሚከተለውን ባውቶማቲክ ለቀቁብኝ(ሎል)

“ ጸሐፊው በማወቅና ባለማወቅ መሐል ተገሽሮ፤ ወይ ተንጠራርቶ በደንብ አላወቀና የጻፈውን ከእውቀት ባህር አልቀዳው ወይ እስኪያውቅና አመዛዝኖ በቅንነት ነገን አሻግሮ ማየት እስኪችል ጠብቆ አልጻፈው በበለው በለው ስንቱን ዘበዘበው ስንቱንስ በዱልዱም አሽሙርና ሽሙጥ ጥላሸት ሊቀባው፤ ከል ሊያለብሰው ዳዳው፡፡ እኔ ለድፍረቱ ወደር አላገኘሁለትም!
በገጽ 24 ላይ የላስታ ገጸ በረከት ባለው ርዕስ ስር “የላሊበላ አዳራሾችን በቃላት ወይም በፊልም ለማስረዳት መሞከር አሪፍ ቅኔን በዱዳ ቋንቋ ለመተርጎም እንደመሞከር ነው የላሊበላ አዳራሾችን ምን ብለን እንጥራቸው? ” ይለናል፡፡
ልብ በሉ እኒያን የተከበሩ የታሪክ ፈርጦች ፤ የኛ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ቅርስ የሆኑትን ፤ በትክክለኛ መጠሪያቸው የቅዱስ ላሊበላ ዉቅር ዓብያተክርስቲያናትን “አዳራሾች” በማለት ያልተገባ ስያ፤ሜ ሲሰጣቸው“

ከላይ የቀረበውን ክምር አንቀጽ ሸከሸክሁት፤ ጠብ የሚል ፍሬ ነገር አልነበረውም፡፡ አረፍተ ነገሮችንና ሐረጎችን እየበለትኩ ደረደርኳቸው፡፡ በቅንፍ ያለው ሳነብ የተሰማኝ ስሜት ነው፡፡

1” በማወቅና ባለማወቅ መሀል ተገሽሮ“( በለው! ምን ማለት ይሆን ? )
2” ተንጠራርቶ“( ማን ላይ ለመድረስ ይሆን?)
3” ስንቱን ዘበዘበው“(መዘብዘብ ማለት እንዴት እንደሆነ አብረን እንመልከት)
3” በዱልዱም አሽሙርና ሽሙጥ ጥላሸት ሲቀባው“ (ምኑን?)
4” ከል ሊያለብሰው ሲዳዳው ”( ክብርት ዶክተር!ቁጥር ሦስትና አራትን ባንድ ላይ ጨምቀው “ ሲያጠለሸው ” ብለው ማለፍ ይችሉ ነበር፡፡)
5“ እኔ ለድፍረቱ ወደር አላገኘሁለትም፡፡”( ወይ ግነት!ወይ ኩሸት! ላሊበላን ተጫርቼ ልግዛው ያልኩ አስመሰሉትኮ !)

ውድ አንባቢ ከዚህ ሁሉ ዘለፋና ፍረጃ በኋላ ሀያሲየ ወደ ነጥቡ ይመጡ ይሆን? አብረን እንከታተል፡፡

6“ ልብ በሉ እኒህን የተከበሩ የታሪክ ፈርጦች” ( የታሪክ ፈርጥነታቸውን ማን ካደ?)
7“ የኛ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ የሆኑትን ” ( ኧረ በህገ ኣምላክ ወደ ወደ ነጥቡ ይግቡልኝ፡፡ )
8 “ በትክክለኛ መጠርያቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን ን “ አዳራሽ“ በማለት ያልተገባ ስያሜ ሲሰጣቸው”

እፎይ ፤ጉዟችን ረጅምና መራራ ቢሆንም ወደ ነጥቡ ደርሰናል፡፡

የላሊበላ ህንጻዎች እኔ እንዳየኋቸው የተራቀቁ አዳራሽ ናቸው፡፡ ህንጻም ናቸው፡፡ ምን ብየ እንድጽፍ ነበር የሚጠበቅብኝ?ድንኳኖች?ስቴድየሞች?
በርግጥ ፤የአዳራሾቹን ቤተመቅደስነት አልካድኩም፡፡ ለምሳሌ “ ቤተመቅደሶቹ እንዴት እንደተሠሩ የሚናገር መጽሐፍ ሳይደርሰን መቅረቱ እንደ እግር እሣት አያንገበግብም?”ብየ ስጽፍ (ገጽ 27)ቤተመቅደስ መሆናቸውን መቀበሌን አያሳይም?

ከተነሣ ላይቀር፤ አንዳንድ የላሊበላ አዳራሾች ሲፈጠሩ ከቤተመቅደስነት የተለየ አገልግሎት እንደነበራቸው የሚገልጡ የምርምር ውጤቶች አሉ ፡፡ በላሊበላ ዙርያ የተመሰገነ ምርምር ያደረገው David W Phillipson , Foundations of an African Civilizationበተባለው መጽሀፉ ያሠፈረውን ከታች አስቀምጨዋለሁ፡፡
The oldest surviving features at Lalibela included rock- hewen and built elements ,sometimes apparently combined , and were not originally created as churches ,although at last some were subsequently altered and converted to Ecclesiastical use.
ገጽ 223)

በመጨረሻ፡፡
ለንጹህ ልብ ሁሉም ንጹህ ነው፡፡ ክፉ ልብ ከዚህ ይለያል፤ በስድብ የተሞላ ዓይን በሣር ቅጠሉ ላይ ስድብ ያያል ፡፡ ላሊበላን “ አዳራሽ አልከው” ብሎ ለነገር የሚቸኩልን ሰው ከዚህ በላይ ምን ሊገልጸው ይችላል??

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

facebook

https://www.facebook.com/

Blog Stats

  • 54,681 hits
Advertisements
%d bloggers like this: