Uncategorized

ወልቃይት ፀገዴና ፀለምት፥ በዐይኔ ካየሁትና ከታዘብኩት በያሬድ ጥበቡ

መጋቢት 1 ቀን 2008 አም

መግቢያ

የዛሬ 39 አመት ግድም ለሶስት አመታት ያህል ከሰኔ 1969 እስከ ሰኔ 1972 አም ድረስ በፀለምት፥ ዋልድባ፥ ቆላወገራና ወልቃይት ውስጥ የኢህአፓ ሰራዊት አባል በመሆን በእግሬ ተጉዣለሁ ። በአማካይ በቀን 5 ሰአት እንጉዋዝ ስለነበር ፥ በአመት 9000 ኪሎሜትር፥ በሶስቱ አመት ቆይታዬ 27000 ኪሎሜትር ያህል መንገድ ተጉዣለሁ ማለት ነው። ዛሬ እነዚህ አካባቢዎች በነዋሪው ህዝብና በአገዛዙ መሃል የማንነት ጥያቄ የውጥረት ማእከል ሆነዋል ። ከ39 አመታት በፊት ወልቃይትንና ፀለምትን ሳውቃቸው ምን ይመስሉ እንደነበር የማስታውሰውን ያህል ባካፍልስ ብዬ ብእሬን አነሳሁ ።

የምሰጠው ምስክርነትና የማነሳው ክርክር በማውቀው የመልክእምድር አቀማመጥና የህዝቡ ባህል ላይ የተመሰረተ ነው ። የክርክሬ ማጠንጠኛ፥ እንደ ተከዜ አይነት ታላላቅ የተፈጥሮ ወሰኖች በትናንሽ አይዲዮሎጂዎች ቢገሰሱ ከፍተኛ ውዝግብና አለመረጋጋትን
ስለሚያስከትሉ ጥንቃቄን ይሻሉ የሚል ነው ። በተጨማሪም የተከዜን አይነት የተፈጥሮ ወሰኖች ተሻግረው ከአጎራባች ህዝብ እቅፍ ውስጥ የተስተናገዱ ማህበረሰቦች፥ ያስጠጋቸውን ህዝብ ማንነት የመፈታተን መብት ሊኖራቸው አይገባም ብዬም ለመከራከርም ነው ።

ተከዜ ፥ ታላቁ የተፈጥሮ ወሰን
ወሎና ጎንደርን አያዋሰነ ተከዜን ከሚቀላቀለው የፅላሬ ( ጥራሪ) ወንዝ ጀምሮ፣ ትግራይንና ወሎን፣ ትግራይንና ጎንደርን፣ ከዚያም ጎንደርንና ኤርትራን የሚያዋስነውን ታላቁን የተከዜ ወንዝ፣ ከምንጩ ከኩል መስክ ተነስቶ ሱዳን ከሰላ አካባቢ እስኪገባና አትባራ ተብሎ
እስኪሰየም፣ በነዚህ በተጠቀሱት የክፍላተሃገራት ወሰኖች ሁሉ በእግሬ ያቆራረጥኩና በሁለቱ አይኖቼ ያየሁ ሰው በመሆኔ፣ ስለ ድንበር አካለዩ ተከዜ መናገር ከሚችሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መሃል ነኝ ።

በመጀመሪያ ተከዜን ያየሁት በሰኔ 1969 ሀይል 17 የምትባል የኢህአፓ ሰራዊት አባል ሆኜ፣ ከአሲምባ ትግራይ ተነስተን ወደ ፀለምት ጎንደር ባደረግነው ጉዞ ወቅት ነው ። የግባን ወንዝ ስንሻገር የኮንጎ ላስቲክ ጫማዬን የሰኔ ውሃ ሙላት ይዞት ሄዶ ስለነበር፣ በጨርቅ
በተጠቀለለ እግር እየተጓዝኩ ነው ተከዜን የተሻገርኩት ። ወደፀለምት መሻገሪያው በጣም ረበዳ ሸለቆ ስለነበር፣ የተከዜን ገመገም ጠዋት መውረድ የጀመርን፣ ወንዙን ተሻግረን አቀበቱን እስክንወጣ ቢያንስ የስድስት ሰአት መንገድ እንደወሰደብን ትዝ ይለኛል ። እጅግ አድካሚ ጉዞ ነበር ። ከሰአት በኋላ ፀለምት ውስጥ ከሚገኝ መንደር ደረስን ። ከፀሀይመግቢያ አቅጣጫ ታላቁ የአቤር ተራራ ቁልቁል በንቀት ይመለከተንም፣ ያስፈራምእንደነበር ትዝ ይለኛል ። ቁልቁል ወደመጣንበት የተከዜ ሸለቆ የሚገፈትረን ነበር የሚመስለው ። ልክ እንደኛ ሁሉ አስቸጋሪውን የተከዜ ሸለቆ አቋርጠው የመጡ የትግራይሰዎች ከነባሩ የስሜን ሰው ጋር የፀለምትን ማህበረሰብ መስርተው፣ ትግርኛም አማርኛም እየተናገሩ ይኖራሉ ። ከአዴት፣ ከአቢይ አዲ፣ ከአክሱም አካባቢ ከጉማ አምልጠው ወይም የሰው ህይወት አጥፍተው፣ ወይም ችግር አብሮአቸው ፀለምት ላይ ከወባና ወበቅ ጋር እየታገሉ፣ የተከዜን ገመገም ይዘው የሰፈሩ የትግራይ ሰዎች ብዙ ናቸው ። ጎንደር መሬት ላይ የሰፈሩ ትግራዋዮች።

አሲምባ የነበረው የኢህአፓ ሰራዊት በየካቲት 1970 አም “ትግራይ ለትግሬዎች” በሚል በህወሐት ድንገት ያልታሰበ ጥቃት ተሰንዝሮበት በብዙ መቶ ለሚቆጠሩ ጓዶች ሞትና መቁሰል ምክንያት ሆነ። ትግራይ ውስጥ መቆየት ስላልተቻለም ወደ ኤርትራ ማፈግፈግ የግድ ሆነ። ሰራዊቱ በጀብሀ አስጠላይነት ስር ስድስት ወራት ተኮምቢያ አካባቢ፣ ጋሽ ወንዝ ዳር ከከረመ በኋላ መሰከረም 1971 ላይ ወደ ፀለምት ሲመጣ፣ የተከዜን ወንዝ ለመሻገር ስንት መከራና ችግር ማለፍ ነበረበት ። ተከዜ እስኪጎድል ኤርትራ ውስጥ በነበረው ቆይታ ወቅት በረሃብ የተነሳ የሰንሰል ቅጠል እንደ ጎመን እየቀቀለ ተመግቧል፣ ጋሽ ወንዝ እያላጋ ያመጣውን የግመል ሬሳ ስጋ በልቶ በተቅማጥ ተሰቃይቷል ። ፀሊም ቤቶች የሚኖሩበትን የወልቃይት ቆላ መዘጋ አቆራርጦ ዛሬማ ወንዝን ተሻግሮ፣ በዋልድባ ገዳም አልፎ ፀለምት መምጣት ነበረበት። ከዋልድባ ወደፀለምት ለመሻገር ግን ወደ ተከዜ የሚገብረው የእንስያ ወንዝ የማይበገር ስለነበር፣ ሰውና አጋሰስ የሚያሻግር ከብረትና ሲሚንቶ የተሰራ አነስተኛ ድልድይ ፀለምት ያለው የሪጅን አመራር አዘጋጅቶ መጠበቅ ነበረበት ። ይህ ሁሉ አበሳ ታይቶ ነበር ሰራዊቱ ከመንፈቅ እንግልት በኋላ ፀለምት የደረሰው ። ፀለምት እንደደረሰም ደርጉ ወረራ አዘጋጅቶ ጠበቀው ። ያንን መመከት የግድ ነበር ። ከደርጉ ጋር የሚደረጉት የመከላከል ውጊያዎች እንደተጠናቀቁም፣ የአሲምባውና የጎንደሩ ጦር
እንዲዋሃድ ተደረገ በዚያን ዘመን ቋንቋ ተቅሊጥ ይባል ነበር፣ አረብኛ ሳይሆን አይቀርም፣ ከኤርትራ ግንባሮች ከወረስናቸው የሽምቅ ቃላቶች መሀል መሆኑ ነው ።

ወልቃይትን እንዳየሁት

የሰራዊቱ ውህደት እንደተፈፀመ፣ እኔ አዲስ በሚከፈተው ሪጅን አራት ውስጥ ተመደብኩና፣ በመጀመሪያ ቆላወገራን ከፀለምት የሚያገናኘውን መስመር ለማለሳለስ እስከ ጃኖራና አጅሬ ድረስ ተጓዝን ። ከዚያም መልስ ወልቃይትን ከኢዴህና ደርጉ ቁጥጥር ነፃ ለማድረግ፣ ከተማይቱን አዲ ረመፅን ለመቆጣጠር ኦፐሬሽን ተዘጋጀ ። ተልእኮውም በቀላሉ ተፈፀመ ። ወልቃይትን ማስተዳደርም ጀመርን ። በሥነምግባራችን ከኢዴህ ቀማኛ ሰራዊትም ሆነ ከደርጉ ማዳፋት ተግባር እጅግ የተሻልን ብቻም ሳይሆን፣ የወልቃይት ህዝብ በመቶ አመታት ታሪኩ ሰምቶትና ገምቶት የማያውቅ ህዝብን አገልጋይ ሰራዊት ሰለነበረን፣ ሊወደንና ሊያፈቅረን ጊዜ አልወሰደበትም ። ቤቱን፣ ማእዱን፣ ጎተራውን ከፍቶ በፍቅር ተቀበለን ። ፍርሃቱ ጥለነው እንዳንሄድ ብቻ ነበር ። የህዝብ አስተዳደር ኮሚቴዎች እያቋቋምን፣ ወንጀለኛ እየቀጣን፣ ቀማኛ እያደንን በሄድን ቁጥር፣ “ፈጣሪ ይህን መልካም አሳይቶ መልሶ አይነሳንም” የሚል የመተማመን ሃሳቡን ህዝቡ ያካፍለን ጀመር ።

የኢህአፓ ተዋጊ ክንፍ የአንዲት አሃዱ ወይም ጋንታ የፖለቲካ ኮሚሳር በመሆን ከፅልእሎ እስከ ቀፍቲያ ፣ ከአዲ ረመፅ እስከ አዲ ጎሹ የህዝብ አደራጅ በመሆን ከወልቃይት ህዝብ ጋር ኖሬአለሁ። ከመሶባቸው ተመግቤአለሁ፣ መደባቸው ላይ ተኝቻለሁ፣ በልጆቻቸው
ሠርግ ታድሜአለሁ፣ በለቅሶና አጎበራቸው ላይ ተቀምጫለሁ። አስተምሬአለሁ፣ ቀስቅሻለሁ ። ከኢዴህ ጋር ሆነው፣ ወያኔን ሲታገሉ ስለከፈሉት መስዋእትነት ሲተርኩ አድምጫለሁ። “ገዳይ ደደቢት ፣ መጠጊያ ድንጋይ በሌለበት”ብለው ሲፈክሩ ተመልክቻለሁ ። ብቻዬንም አልነበርኩም፥ በመቶ የሚቆጠሩ አብረውኝ የነበሩ ታጋዮች ዛሬም በአሜሪካ ይገኛሉ ። የትግራይ ልጆች የነበሩም ብዙ ናቸው ። እንዲያውም ህዝብ በማደራጀቱ ስራ የበለጠ እነርሱ ተመድበው ስለሰሩ፥ የተሻለ መመስከር ይችላሉ ። ወደ አሲምባ ካቀናሁበት ከጥር 1969 ጀምሮ፣ በትግራይም ሆነ ጎንደር ካየሁዋቸው በሺህ ከሚቆጠሩ መንደሮች፣ የወልቃይት መንደሮች በሶስት ነገሮች ጉልህ ልዩነት ነበራቸው ።

አንደኛው፣ ከፍተኛ የሆነ የቆርቆሮ ቤቶች ከምችት ያሉባቸው መንደሮች ብዙ ነበሩ ። በተለይ ከአዲ ረመፅ ወደ ቀፍቲያ መሻገሪያ አቅጣጫ ያሉት መንደሮች፣ እነ ብላምባ ሉቃስና ብላምባ ቅርሺ የመሰሉት ማህበረሰቦች የሳንቃ ወለል የሌላቸው ከመሆናቸው በቀር፣
በስርአት የተገጠሙ የተላጉ በሮችና መስኮቶች ያሉዋቸው፣ የመኝታ ክፍሎቻቸው የተለዩ፣ የቦንዳ አልጋዎች ያሉዋቸውና በዘመናዊ የቤት እቃዎች የሚገለገሉ ነበሩ ። ወተቱ፣ ቅቤው፣ እርጎው፣ ጠላው እንደ ልብ ነበር ። ሴት ወይዘሮው ንፁህ የሚለብስ፣ ወንዱ አውቶማቲክ
ጠብመንጃ የታጠቀ የጠገበና የኮራ ህዝብ ነበር ።

ለሁለተኛ ጊዜ ተከዜን የተሻገርኩት ከአዲ ጎሹ አካባቢ ወደ ኤርትራ መሻገር በተገደድኩበት ወቅት ነው ። ቀኝ እግሬ ላይ መጅ ወይም callus አብቅዬ መራመድ ተቸግሬ ስለነበር፣ የሰራዊታችን ሀኪሞች የነበሩት ስእለና መልአኩ ቀዶጥገና አድርገውልኝ ማገገም ላይ
በነበርኩበት ወቅት ነበር ወያኔ ወልቃይትን የወረረው ። በየቦታው ተበታትነን የነበርን ጥቂት ታጋዮች፥ ከአዲ ረመፅ ወጣ ባለች መንደር ስለወረራው ሁኔታና ሰራዊታችንም የት እንደሚገኝ ከአርሶአደሮቹ ለማጣራት በምንሞክርበት ጊዜ እዚያ መንደር ውስጥ እንደምንገኝ ወያኔ ስላወቀች አመሻሽ ላይ ታጋዮቿን ልካ በተኩስ አጣደፈችን ። ተኩስ በሌለበት አቅጣጫ እያፈገፈግን ተበታተንን ። ብላምባ ሉቃስ አድሬ የበለጠ መረጃ ሳሰባስብ፣ አዲ ጎሹ አካባቢ የነበሩት ተዋጊ አሃዱዎች ወደ ኤርትራ መሻገራቸውን አስተማማኝ ወሬ ሰማሁ ።
ከሌሊቱ በአስር ሰአት ላይ ተነስቼ ገበሬዎቹ ወደቆላ እርሻቸው በሚወርዱበት አሳቻ ቁልቁለት ከደጋው መሬት ወደ አዲ ጎሹ አቅጣጫ ወደሚወስደው በረሃ ወረድኩ ። ድንገት የወያኔ አባላት ቢይዙኝ ወደኤርትራ ጠብመንጃ ለመግዛት እንደሚሄድ የጠገዴ ነዋሪ በመንገድ ላይ ትብብር እንዲደረግልኝ የሚያሳስብ ባለማህተም ደብዳቤ ይዤ የኢህአፓ ሰራዊት አባልነቴን የሚጠቁሙ ቁሶችን በሙሉ አሳዳሪዎቼ ጋ ትቼ ነበር ። ከደጋው ወርዶ ሰው የማይኖርበትን በረሃማ ስፍራ ብቻ ይዞ መጓዙ ከፀሀዩ ቃጠሎና ከውሃ እጦቱ ጋር ተዳብሎ መቋቋም
የሚቻል አልነበረም ። ሆኖም ከአስር ሰአት ያህል የእግር ጉዞ በኋላ ከተከዜ ወንዝ ደረስኩ ። ለመጀመሪያ ጊዜም ለላንቃዬ ማርጠቢያ የሚሆን ውሃ አግኝቼ ጠጣሁ ። ከወንዙ ማዶ እረኞች ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ተመለከትኩ ። ተሻግሬም ተገናኘኋቸው ። ኤርትራውያን
እረኞች ነበሩ ። በጋይት የሚባሉ ላምና በሬዎቻቸውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምናውቃቸው ለየት ያሉና እጅግ የደለቡ ነበሩ ።

አዳር ከኤርትራ እረኞች ጋር

እረኞቹ በረሃብና ጥም መጎዳቴን ሲያዩ በእንጨት ጮጮ ከያዙት ወተት አጠጡኝ ። አብሬያቸው አድሬ በበነጋታው መንገዴን ብቀጥል እንደሚሻልና፣ የኤርትራ መንደሮች እስክደርስ የብዙ ሰአት እግር መንገድ ስለሚቀረኝ ልቸገር እንደምችል ነገሩኝ ። በሃሳባቸውም ተስማማሁ ። ፀሀይ ከማዘቅዘቋ በፊት ከብቶቻቸውን ወደነፋሻማው ዳገት መንዳት ጀመሩ ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ላሞችና በሬዎች በአንድ ላይ ሲታገዱና ሲጠበቁ ሳይ የመጀመሪያዬ ነበር ። ወደ በረታቸው የሚያመሩበት ዳገት ለከባድ መኪና የተሰራ ጥርጊያ
ይመስል ነበር ። ዳገቱን ለአንድ ሰአት ያህል ከወጣን በኋላ ከከብቶቹ በረት ደረስን ። እረኞቹ ከብቶቹን በረት ውስጥ ካስገቡ በኋላ፣ ትልቅ የካምፕ እሳት ማዘጋጀት ጀመሩ ። ከተከዜ ወንዝ ዳርቻዎች የሰበሰቧቸውን ጠጠሮች በማሽላ ሊጥ እየጠቀለሉ የሚነደው እሳት
ውስጥ ይዶሉ ጀመር ። ብርኩታ ተብሎ የሚጠራው እራታቸው እንደሆነ ነገሩኝ ። ሆዴ እስኪቆዘር ብዙ ብርኩታ በላሁ ።

የምግብ ማብሰያ ብረትድስት ስላልነበራቸው እሳት ውስጥ የጋሙና ፍም የመሰሉ የወንዝ ዳር ጠጠሮችን በመቆንጠጫ ባላ እንጨት እያወጡ አዲስ የታለበው የጮጮ ወተት ውስጥ እያስገቡ ቸስ ብሎ ሲቀዝቅዝ ፣ ያንን ጠጠር ወደእሳቱ መልሰው እየወረወሩ ሌላ የጋለ ጠጠር ጮጮው ውስጥ በመጨመር ወተቱ እንፋሎት ማውጣት እስኪጀምር ድረስ እየተቀባበሉ አፈሉት ። ከዚያ የፈላው ወተት ላይ የማሽላና በቆሎ ዱቄት በመጨመር ገንፎ አገነፉ ። እንዴት እንደሚጣፍጥ ማመን አትችሉም ። ገንፎ በልተን እንደጨረስን፣ ከሰው ወደሰው ጮጮው እየተላለፈ፣ አዲስ የታለበ ትኩስ ወተት ፉት ስንልና ስናወራ አምሽተን፥ እዚያው እሳቱ ዳር ተኛን ። በጣም ከሩቅ ሃገር፣ ለሳምንታት ተጉዘው መምጣታቸውንና፣ እስከ ክረምቱ ወራት ድረስም ተከዜ አካባቢ እንደሚቆዩ አጫወቱኝ ። በማግስቱ ተሰነባብተን የተከዜን አቀበት መውጣቴን ስቀጥል፣ እነርሱም ትተውት ወደመጡት ተከዜ ለምለም ሳር ፍለጋ ከብቶቻቸውን ይዘው ወረዱ ።

ከኤርትራ ወደ ፀለምት መልስ

ከሁለት ቀናት በኋላ የጀብሃ ሚሊሺያዎች ለአካባቢው የፀጥታ ሹም ለነበረው ለጆርጅ ወስደው አስረከቡኝ ። ገና ስንተያይ ከጆርጅ ጋር ኮከባችን ገጠመ ። ለአመታት ተለያይቶ እንደተገናኘ ጓደኛ ማውራትና መከራከር ጀመርን ። ስለጀብሀ የማላውቃቸውን ብዙ ነገሮች
አጫወተኝ ። ለካስ ጀብሃ፣ ተራ የእስልምና አክራሪዎች ድርጅት ሳይሆን ፣ በውስጡ የአንጃዎችን መኖር የሚቀበል፣ ከባዚስቶች እስከ ሊበራሎች በአንጃ በአንጃ ተደራጅተው ለጋራ አላማ የሚሰሩበት ግንባር ነበር ። ስብዞዎቻችን ኢህአፓ ውስጥ ሳለን ይህን ዴሞክራሲያዊ ገፅታቸውን ፈፅሞ አናውቅም ነበር ። ጆርጅ ኤርትራ ከገባችው የኢህአፓ አሃዱ ጋር አገናኘኝና፣ ወደፀለምት ለመመለስ ተወሰነ ።
ወልቃይት በወያኔ ስለተያዘ፣ በዚያ ማለፍ የሚታሰብ አልነበረም ። እስከ ዛሬማ ወንዝ መገናኛ ድረስ ዋልድባ ገዳም እስክንቃረብ የተከዜን ወንዝ ተከትለን ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ልንሄድ ወሰንን ።

ቀኑን ሙሉ ተከዜን ግራና ቀኝ እያቆራረጥን ውለን አመሻሽ ላይ ደከመን ። ረሃቡም የሚቻል አልሆነም ። መጋቢዎች ከተከዜ ወጥተው ምግብ ፍለጋ ወደመንደሮቹ እንዲሄዱ ታቀደ ። ይህን አደገኛ ተልእኮ የሚፈፅም ፈቀደኛ የሰራዊት አባል ማግኘት አልተቻለም ። በመጨረሻ እኔና አንድ ስሙ የተዘነጋኝ የአምባ ማድሬ አርሶአደር ታጋይ ሄደን ምግብ ለመሰብሰብ ፈቃደኛ ሆንን ። አመሻሽ ላይ መንደሩ ውስጥ የወያኔ ጦር አለመኖሩን አጣርተን ገባን ። ከነዋሪውም ምግብ እንዲሰበሰብልን አደረግን። ብዙም ሳንቆይ የህወሐት ታጋዮች መጥተው በተኩስ ያጣድፉን ጀመር ። ሁለታችንም ምግቡን ትተን ላለመሸሽና የተኩስ አፀፋ ላለመስጠትም ወሰንን። የተሰበሰበውን እንጀራና ወጥ በነጠላዎቻችን ላይ እያሰርን ተኩስ የሌለበትን አቅጣጫ መቃኘት ያዝን። እንጀራና ወጡን በነጠላችን አስረን ከተሸከምን በኋላ የተኩስ ክፍተት በነበረበት ቀዳዳ ድምፃችንን አጥፍተን ተሰለብን ። ወደተከዜ የሚያወርደውን ገመገም ተከትለንም ከጓዶቻችን ተቀላቀልን፣ እራታቸውንም አበላን ።

ስለ ወልቃይት ምስክርነት

ቀደም ብዬ ወልቃይቴ ሃብታም ነው ብዬ ነበር ። በሌላው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ያላየኸው የተሻለ ህይወት ወልቃይት ከየት አመጣው ትሉ ይሆናል ። ስለ ወልቃይት ስናወራ፣ ወልቃይቴው ማለት ደጋው ላይ የሚኖረው በፅልእሎ፣ ሽሬላ፣ ደጀና፣ አዲ ረመፅ፣ የብላምባ መንደሮች፣ ብርኩታና ቀፍቲያ እንዲሁም ቆላው ላይ አዲ ጎሹ የሚኖረው ወልቀታይ ነው ። ይህ ህዝብ በቆርቆሮ ቤቶች በተሻለ ህይወት መኖር ብቻ ሳይሆን፣ አልፎ አልፎም የእርሻ መኪናዎችም ያሏቸው ጥቂት ባለሃብቶችም ነበሩ ። ቆላ መዘጋው ላይ ከወባና ጊንጥ እንዲሁም ከቆላው ወበቅ ጋር እየታገለ የሚኖረው የፀሊም ቤትና የትግራይ ስደተኛ፣ የደገኛው ወልቃይቴው አገልጋይና ተጠማኝ (share cropper) በመሆኑ፣ የወልቀታዩ መሬት ላይ ከሚያርሰው አዝመራ አካፍሎ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ፣ የደገኛው ሃብት አንዱ ምንጩ ከዚህ ተጠማኝ አራሽ የሚሰበስበው ሰብል ነበር ። የ1966ቱ አብዮት መጥቶ የሁመራ እርሻ ስራቸው እስኪተጓጎል
ድረስም፣ የወልቃይት ሰው ሁመራ ላይ የሰሊጥ እርሻ ባለቤት ስለነበር፣ በቅድመ አብዮት አመታት ያካበተው ሃብት ብዙ ነበር ። ከሃብታቸው ብዛት እንደ ቀኛዝማች ገብሩ ያሉ ሃብታሞች ሰራዊታችን በሰፈራቸው ሲያርፍ፣ አመራር አባላቱን ጠርተው እንደ እናትና ልጅ አይነት ፋብሪካ ውስጥ የተመረቱ መጠጦችን እስከመጋበዝ የሚችሉ ሰዎች ነበሩባቸው ።

ሁለተኛው ወልቃይትን ልዩ የሚያደርገው ነገር፣ በየመንደሩ ከፍተኛ የሆኑ የእድሜ ባለፀጋዎችና፣ ጎንደርና አዲስ አበባን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ገዳሪፍ ወይም ካርቱምን ደጋግመው የጎበኙ ሰዎች በብዛት ይገኙባቸው ነበር ። ብላምባ ሉቃስ ውስጥ የሚኖሩ አቶ ጥላሁን
የሚባሉ የቭላድሚር ሌኒን መንታ የሚመስሉ ሰው አንዱ የማስታውሳቸው ነበሩ ። ደጀና ውስጥ የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩት የጄኔራል አሰፋ አያና አጎት የሆኑ ግራዝማች መስፍን የሚባሉ ሌላ ምሁርና የታሪክ ሰውም አስታውሳለሁ ። ሁሌም ብዛታቸውና፣ በአንድ ቦታም
ተከማችተው መገኘታቸው ይገርመኝ ነበር ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ጓደኛዬ የነበረው አንዳርጋቸው አያልነህ ስለወልቃይት ሃብትና ወንዳወንድነት (ብረት ወዳድነት) ያወራን የነበረውን ለማመን እንቸገር እንደነበር አስታውስና፣ ኋላ የአንዳርጋቸውን የትውልድ
መንደር ቃቃን (በትክክል ካስታወስኩ ከአዲ ረመፅ በእግር የአንድ ሰአት ተኩል መንገድ ቢሆን ይመስለኛል) ስጎበኝ ከታዘብኩት ጋር ሳመዛዝን፣ ሁሌም ይደንቀኛል ።

ሌላው ወልቃይትን ከብዙ ሌሎች ህዝቦች የሚለየው፣ የለት ከለትና የስራ ቋንቋው ከማንነቱ ጋር የተለየ መሆኑ ነው ። በየእለቱ ወልቀታዩ እርስ በርሱም ሆነ ከተጠማኝ ገባሮቹ ትግሬዎች ጋር የሚገለገልበት ቋንቋ ትግርኛ ነው ። ከፈለገም አማርኛን ይጠቀማል ። ባለ
ሁለት ቋንቋ ህዝብ ነበር ። ሆኖም በትግሪኛ ልጁን መዳርም ሆነ፣ ወዳጁ ሲሞትበት በትግሪኛ ማልቀስ ግን አይሆንለትም ። የሰርግ ዘፈኑና ለቅሶው፣ ፉከራው፣ ሽለላው፣ የመጫቷ አንቀልባ እሹሩሩ ዜማም ሆነ፣ የፈጪታዋ እንጉርጉሮ አማርኛ ነው ። የሚያስገርም
የሚያስደምም ኩነት ነው ። ወልቃይቴው ትግሪኛ ይናገር እንጂ ፈፅሞ የትግራዋይ ስነልቡና የሌለው፣ እራሱን እንደ ኩሩ ጎንደሬ የሚያይ ጅንን ነው ። እንዴት ሊሆን ቻለ? ምናልባት ወልቃይቴው ለህይወቱ የሚያስፈልገውን የምርት ሂደት የሚያከናውኑለት የቆላ መዘጋ ፀሊም ቤቶችም ሆኑ ተጠማኝ የሆኑት የትግራይ ስደተኞችን ለማናገርና፣ ምርቱ ሳይተጓጎል በሰላም ለመጨረስ አስፈላጊ የሆነው የትግርኛ ቋንቋ፣ የእለት ተለት ህይወቱን ተፅኖ አድርጎበት ሊሆን ይችላል፣ ወይስ በሌላ ምክንያት? ምርምርን የሚሻ ጉዳይ ይመስለኛል ።

ወልቃይትና ነፃ የትግራይ ሪፐብሊክ ጥያቄ ትስስር

ወያኔ የነፃ ትግራይ ሪፐብሊክ ማቋቋም አላማ በነበረው ሰአት፣ አንደኛ ከውጪው አለም የሚያገናኝ መስመር ፍለጋ፣ ከፖርት ሱዳን ወደብ ጋር የሚያገናኝ ወሰን በመፈለግ፣ ሁለተኛ፣ ትግራይ የሶስት ሺህ አመታት ስልጣኔና መሬቱ ያለእረፍት ሲታረስ በመኖሩ ምርቱ እየደከመ የመጣ በመሆኑና በአንፃሩ ወልቃይት/ሁመራ ሰፊ ያልታረሰ ድንግል መሬትና እንደ ሰሊጥ አይነት ካሽ ክሮፕ ሰብል የሚያመርት በመሆኑ፣ ነፃ ለምትወጣው ትግራይ ትልቅ ለም መሬት ስለሚያስገኝ፣ ወልቃይትንና ሁመራን ለመጠቅለል ታቀደ ። የህወሐት መሪዎች ፀገዴ የቢትወደድ አዳነ አገር መሆኑን ያውቁ ስለነበር፥ በትጥቅ ትግሉ ማጠናቀቂያ አመታት ክሳድ
ግመል ውስጥ ቤዝ አምባ የመሰረቱ ቢሆንም፥ የትግራይ ነው ሲሉ ሰምቼም አላውቅም ። በግርግር የጨመሩት መሬት ነው ። የትግራይን ነፃ ሪፐብሊክ የማቋቋም አላማ ትተናል በሚባልበት ወቅት፣ ወልቃይትንና ፀገዴን ትግሬ የማድረግ ህልሙ ግን አልቆመም ። ለምን?

በ1972 አጋማሽ ላይ ወያኔ ወልቃይትን ለመውረር ሲመጣ በመጀመሪያ የኢህአፓን ጦር መደምሰስ ነበረበት ። የኢህአፓ ሰራዊት ከየሪጅኑ የተውጣጣ ሃይል ሰብስቦ ደባርቅና ዳባት አካባቢ ለመንቀሳቀስ አብዛኛውን ሀይሉን ከወልቃይት ባራቀበት ወቅት ህወሐት ድንገት ከፍተኛ የሰራዊት ሀይሉን ይዞ ወልቃይትን ወረረ ። ከያዘ በኋላ ለማስለቀቅ ቀላል አልሆነም ። ብዙ የኢህአፓም ሆነ የወያኔ የሰራዊት አባላት የተሰውበት የሽሬላና የቆላ መዘጋ ጦርነቶችት የተካሄዱ ቢሆንም፣ ወያኔን ከወልቃይት መንቀል ግን አልተቻለም ። እንደገና ወደፀለምት ማፈግፈግ ተገደድን ።
ወያኔ ከ1972 አጋማሽ ጀምሮ የወልቃት ይዞታውን ለማጠናከር በከፍተኛ ደረጃ የመሬት ችግር ያለበቸውን ትግሬዎች እያመጣም አሰፈረ ። ባለፉት 30 አመታት እስከ 80 ሺህ ህዝብ ከትግራይ አምጥቶ እንዳሰፈረ ይነገራል ። አዲስ አበባም እንደገባ ከምእራባውያን ጋር
የሰራዊት ቅነሳ ለማድረግ ሲስማማም፣ ለቅነሳው ማካሄጃ የተሰጠውን ድጎማ በመጠቀም፣ ተቀናሾቹን የወያኔ ሰራዊት አባላት በቀፍቲያና ዳንሻ አካባቢ 30 ሺህ የቀድሞ ወያኔ አባላትን ከነትጥቃቸው አስፍሯል ። ህወሐት ነባሩን የወልቃይት ህዝብ በአዲስ ስደተኛ ካጥለቀለቀና ፣ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ በአመፅ ከቀየረ በኋላ “ብትፈልጉ ህዝበ ውሳኔ ወይም ሪፍረንደም ይካሄድ” ፥ ወይም
ሲነሽጠው “ወደ ትግራይ ከመጠቅለሌ በፊት ህዝበ ውሳኔ አካሂጃለሁ” ብሎ ያላግጣል ። ይህ ግን ተራ ቧልት ነው ። ከማንኛውም ህዝበ ውሳኔ በፊት ወልቃይት ወደነበረበት መመለስና አሁን በቦታው ላይ ያለው የወያኔ የግፍ አገዛዝ መልቀቅ ይኖርበታል ። ይህ ቅድመ
ሁኔታ ሳይሟላ ስለ ህዝበ ውሳኔ ማውራት አይቻልም ።

የተፈጥሮ ወሰን ይከበር

እኔ የአራዳ ልጅ ነኝ ። ዛሬ ጊኒር ባሌ ወይም ወለጋ ቄለም የሚኖር የኦሮሞ ወጣት በወያኔ አይዲዮሎጂ ተኮትኩቶ “ፊንፊኔ የኔ ናት” በሚልበት ወቅት ይበልጥ የሚያንገበግበኝ ጉዳይ ስላለ፥ የወልቃይት ጉዳይ ላይመለከተኝ ይችላል ። ሆኖም፥ ሁለቱም ጥያቄዎች የተሳሰሩ
ናቸው ። የቁዋንቁዋ ክልል አይዲዮሎጂ የወለዳቸው ። በተጨማሪም የህይወት አጋጣሚ ሆኖ በፀለምት ወልቃይትና ተከዜ ሸለቆዎች ትዳር መስርቼ ስለነበር፥ የእማኝ ቃሌን የመስጠት የህሊና ግዴታ አለብኝ ። ተከዜንም ብቻ ሳይሆን፣ ገባሮቹ የሆኑትን ጥራሬን፣ፍራፍራን፣ እንስያን፣ ዛሬማን ወንዞች ለቀናት ተጉዤባቸዋለሁ፣ አድሬባቸዋለሁ ። የጥራሬን ወንዝ የጓዳዬን ያህል አውቀዋለሁ ብል ማጋነን አይመስለኝም ። ከወያኔ ጋር ድርጅታዊ ግንኙነት ለማድረግ ከሰቆጣ አካባቢ ተነስቼ አንዲት ቦንብ ወይም አንድ ሽጉጥ ታጥቄ ሙሉ ቀን ወይም ሙሉ ሌሊት ብቻዬን ስጓዝ የጥራሬን ወንዝ ብዙ ጊዜ ተሻግሬአለሁ ።

በጥቅምት 1971 ከፀለምት ተነስተን ወደ ቆላወገራ ስንሄድና ወደ ወልቃይት ስንመለስ በዛሬማ ወንዝ ዳርቻዎች ለቀናት ኖረናል ። የሚበላ እህል ስላልነበር፣ ወንዙ ዳር የነበሩትን የሸምበቆ ተክሎች እየቆረጥን ከሸምበቆ አገዳ በተሰሩ ቢላዋዎች የሰንጋ ቁርጥ እየጎመድን በዛሬማ ወንዝ ውሃ እያወራረድን በብስናት አልቀናል ። በስኔ 1972 የፀለምት የኢህአፓ የአርሶአደር ሚሊሺያዎች ሊከዱ ነው ብለው ጠርጥረውን 13 የሰራዊቱን አባላት ካስሩን በኋላ “ሲነጋ እንዳናገኛችሁ” ብለው ሲለቁን፣ ሰኔ 4 ሌሊቱን ሙሉ የፍራፍራ ወንዝን ግራና ቀኝ ስናቆራርጥ አድረን ከፀሐይ ጋር ቀጠሮ ያለን ይመስል ልክ ስትወጣ ከተከዜ ወንዝ ደረስን፣ ተከዜንም ለሶስተኛ ጊዜ አየሁት ፣ ዳግምም ወደ ትግራይ ኣቋረጥኩት ። እንኩዋንስ ተከዜ ገባሮቹ እንኩዋ ፥ ሃያል ነበሩ ። የተፈጥሮ ወሰኖች ።

በእኔ አስተያየት፣ መገናኛና መጓጓዣ አስቸጋሪ በነበረባቸው ዘመናት አንድ ማህበረሰብ ከዘመዶቹ ርቆ፣ በመሃሉ ከሶስት ወራት በላይ የሚያቆራርጠው ተከዜን ያህል ወንዝ ተሻግሮ ኑሮ የሚመሰርተው አስገዳጅ የህይወት ገጠመኞች ሲኖሩት ይመስለኛል ። ራሱን ከጥቃት
ለመከላከል ሲልም ሆነ ራሱን ጠብቆ ለማቆየት፣ የሱን ቋንቋ ከሚናገሩ ህዝቦች ጋር መቆየትን ይመርጣል ። ለዚህም ነው በኢትዮጵያችንም ሆነ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ታላላቅ ወንዞች የህዝቦች ተፈጥሯዊ ወሰን ሆነው የኖሩት። በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በመላው አለም፥ የተራራ ሰንሰለቶች፣ ወንዞችና፣ በረሃዎች ተፈጥሯዊ ወሰን ሆነው የተለያዩ ማህበረሰቦችን አካልለው በሰላም አኑረዋል ። አሁን ህወሐት ያንን አለማዊ አሰፋፈር ነው በቋንቋ ክልል አይዲዮሎጂ መለወጥ የሚፈልገው ። መልክአ ምድር ወይም ጂኦግራፊ በማህበረሰቦች አሰፋፈርና ተፈጥሮአዊ ድንበር ሆኖ ስለሰጠው ግልጋሎትና ስላደረገው ተፅእኖ፥ ለመስኩ ባለሙያዎች እተወዋለሁ ። እኔ ግን በአስር አመት የበረሃ እንግልቴ የታዘብኩት ተፈጥሮ በህዝብ አሰፋፈር ላይ ያደረገውን ተፅእኖ ነው ።

ይህንን ተፈጥሮአዊ የህዝብ አሰፋፈር ሎጂክ በቋንቋ ክልል ፌዴሬሽን ሎጂክ በመተካት፣ ህወሐት በፀለምት በኩልም የብራ ዋሰያንና የዋልድባን ለም መሬቶች ከጎንደር በመዝረፍ ከዛሬማ ወንዝ ምላሽ ያለውን ሃገር በሙሉ፣ ትግርኛ እስከተናገረ ድረስ ትግሬ መሆን አለበት በሚል በጉልበት ወስዷል ። ትናንት ነፃይቱን የትግራይ ሪፐብሊክ በሚመኙበት ሰአት በወጣትነት ትኩስ አእምሮ የነደፉትን ጨቅላ አስተሳሰብ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እየገዙ ባለበት ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ እንደደፈሩ ሳስበው ከወቅቱ ጋር መራመድ ለምን እንደማይችሉና፣ ለምን ከሃቅ ጋር እንደሚላተሙ ሁሌም ይገርመኛል ።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣናቸው ከተወገዱ ጥቂት ወራት በኋላ ፣ ኢዴህ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት) ሲመሰረት፥ የወልቃይትና ፀገዴ መሳፍንትና የሁመራ ባለሃብቶች፣ ሁመራ ላይ ያገለግሏቸው የነበሩትን ከትግራይ የመጡ
የዘመናዊ እርሻ ሰራተኞችን (ወዛደሮችን) አስታጥቀው በደርግ ጦር ላይ ዘመቻ ከከፈቱበት ሰአት ጀምሮ ላለፉት 40 አመታት ከፍተኛ የጦር አውድማ ሆኖ የቆየ አካባቢ ነው ። የታክስ መረጃዎች ተበትነዋል፥ መዝገብ ቤቶች ተቃጥለዋል፥ ታሪኩን የሚያውቁ አዛውንት
አልቀዋል ። ወልቃይት ፀገዴ እምብዛም እረፍትና ሰላማዊ አስተዳደር አግኝቶ አያውቅም ። እኔ ወልቃይት በነበርኩባቸው የ1971 እስከ 72 አመታት ብቻ እንኳ በእኛና ኢዴህ መካከል ሥፍራ ሃፀይ አካባቢ፣ በእኛና ወያኔ መካከል በሽሬላና ቆላ መዘጋ አካባቢዎች ውጊያዎች ተደርገዋል ። ወያኔ አካባቢውን ከተቆጣጠረም በኋላ፣ “ተገደን ትግሬ አንደረግም” የሚለው የትጥቅ ተቃውሞ ቀጥሎ ባለፉት 35 አመታት ከፋኝ፣ አርበኞች ግንባር ወዘተ የሚሰኙ ሃይሎች ከወያኔ ጦር ጋር መቆራቆሳቸውን አላቆሙም ። በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች እካባቢው ተተራምሷል ። የህወሐት “ትግርኛ የተናገር ሁሉ ትግሬ ነው” አይዲዮሎጂ የበለጠ ትርምስና የንብረትና ህይወት ውድመትን የሚያስከትል ነው ።

በእኔ እምነት መፈቀድ የሌለበት፣ ተከዜን አይነት የተፈጥሮ ወሰን ተሻግሮ በሌላ ማህበረሰብ እቅፍ ውስጥ ተጠግቶ የኖረ የወሰን ተጎራባች ህዝብ፣ ካስጠጋው ህዝብ መሬት ላይ ቆርሶ በመውሰድም ሆነ፣ ቁጥሩ ከአስጠጊው መብለጡን እርግጠኛ ሲሆን፣ በህዝበ ውሳኔ
(ሪፍረንደም) ሽፋን ያስጠጊውን ህዝብ መሬትና አስተዳደር መንጠቅ ሊፈቀድለት አይገባም።

ሆኖም ህወሐት በሶሻል ኢንጂነሪንግ ስለሚያምን፣ ይህን ሃሳብ አይቀበልም ። በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ ስለቀየርኩ ማንም አይነካኝም ብሎ እግሩን አንፈራጦ ተቀምጧል ። ሆኖም የወልቃይት ፀገዴ ችግር ውሎ አድሮ ኢህአዴግን ከውስጡ የሚሰረስር ጉዳይ ነው ። እንደ
ኦህዴድ ሁሉ ብአዴንንም ማስሸፈቱ አይቀርም ። የህዝቡን ጥሪና አቤቱታ ተቀብሎ፣ አማራ ነን በማለታቸው ከሚደርስባቸው መበሳበስና እንግልት ሊታደጋቸው ይነሳ ይመስለኛል ። የብአዴን መፈተኛው ደረሰ መሰለኝ ። ከኦህዴድ መማር ይችላል ። የወያኔ ተባባሪና መንገድ መሪ ያለመሆን አማራጭ ከፊቱ ተደቅኗል ። በጣም ትንሽ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ጉዳይ ይመስለኛል ። የህወሐት ዐይንና ጆሮ ላለመሆን እንደ ኦህዴድ መወሰን ። አዎን ይቻላል!

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

facebook

https://www.facebook.com/

Blog Stats

  • 54,681 hits
Advertisements
%d bloggers like this: