Uncategorized

የት ነው ያለሁት? እንዲሁ ይጨንቀኛል! – ነፃነት ዘለቀ

ሰሞኑን ልክ አይደለሁም፡፡ መላ ሰውነቴ ልከ አይደለም፡፡ እጅግ ይጨንቀኛል፡፡ ያ ደደብ ደም ብዛት የሚሉት በሽታ ሊይዘየኝ ይሆን እያልኩም እጨነቃለሁ፡፡ የጭንቀት ጥበቴን መነሻ ግን አውቀዋለሁ፡፡ መፍትሔ የሌለው መሆኑ ስለሚሰማኝ ግና እየባሰብኝ እንጂ እየቀለለኝ ሲሄድ አይታይም፡፡ በተረቱ “የጨው ተራራ ሲናድ ብልህ ያለቅስ፣ ሞኝ ይስቅ” ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ የቁም ሞት የምንበሳጭና ተበሳጭተን የበኩላችንን አስተዋፅዖ የምናደርግ በጣም ጥቂቶች ነን – እኔን ሳይጨምር፤ ለኔ መጨነቄ ብቻ ይበቃል፡፡ ሀገር ቤት በተለይም አዲስ አበባ ላይ ያለን ዜጎች ከቁጥራችን በላይ የሆነ የሰላይና የሆድ አደር ግሪሣ ስለከበበን ጥላችንንም እንፈራለን – ስለዚህም ማድረግ ቀርቶ ለማድረግ ማሰባችንም የሚደረስብን ይመስለናልና ከማሰብም ተቆጥበናል – (የጆርጅ ኦርዌል ‹1984› መጽሐፍ ጨርሶታል)፡፡ ደርግ አመቻችቶት የሄደው የፈሪነት መንፈስ ሀገር ምድሩን አጥልቶበት የወንድነት ምልክታችን ሁሉ ወዳንጀታችን ገብቶ አንዳንዶቻችን ለመሽኛ እንኳን ፈልገን ልናገኘው አልቻልንም፡፡ “አንዳንዶቻችን” እያልኩ ባይሆን አባዘራፎችን ላግባባ እንጂ፡፡

 

ፎቶ ፋይል

በአሁኑ ወቅት ሀገር አለችኝ አልልም፡፡ ዘረኝነቱ፣ አድልዖው፣ መታሰር መገረፉ … አይደለም የአሁኑ ችግር፡፡ እነዚህ የጠቃቀስኳቸው ችግሮች የዱሮ ናቸው፤ በጣም የተለመዱ፡፡ የአሁኑ የባሰ ነው፡፡

ደርግ ሥጋን ይገድል ነበር፡፡ ወያኔ ግን ሥጋን መግደል ብቻውን ስለማያረካው ከዚህ ደረጃ አልፏል፡፡ እናም ወያኔ የሚገድለው መንፈስን ነው – የሰይጣን ጠባይም ይሄው ነው፡፡ ወያኔ የሚገድለው ቅስምን ነው፡፡ ወያኔ የሚገድለው ኅሊናን ነው፡፡ ወያኔ ቢገድል ደስ የሚለው ነፍስንም ጭምር ነበር – ይህ ግን የማይቻል ሆኖበት ተቸግሯል፡፡ ስለዚህም መግደል የሚችለው የኛነተቻን ክፍል ተፈቅዶለት አለርህራሄ እየገደለን ነው፡፡

ሥጋን መግደል ቀላልና እርካታውም ጊዜያዊ መሆኑን ሰይጣናቱ ወያኔዎች በሚገባ ያውቃሉ፡፡ አንድን ሰው በጥይት ደብድበው በደቂቃዎች ውስጥ መግደል ቢችሉም ያን ቢሞቱ አያደርጉትም፡፡ በርሀብ ወይም በበሽታ ወይም በሥነ ልቦናዊ ጭንቀት ቀስ ብሎ እንዲሞት በማድረግ መዝናናትን ነው የሚወዱት፡፡ ድመት በግዳይዋ ተዝናንታና ሰውነቷን አሟሙቃ ዐይጥን እንደምትበላት ወያኔም በጠላትነት የሚፈርጀውን አካል ወይም ግለሰብ አመንምኖና አክስቶ በማሰቃየት ይገድላል፡፡ ይህ ደግሞ የፈሪዎች ፈሊጥ ነው፡፡ ጀግና በጀብድ እንጂ በዕብሪት አይኩራራም፡፡ ጀግና በርህራሄ እንጂ በጭካኔ አይገድልም፡፡ የርህራሄ ግድያን ለማወቅ ወያኔዊ አገዳደልን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከእሥር የተፈቱ ግን በቁማቸው የሞቱ እነ እንትናን ማየቱ ወያኔ በቁም በመግደል ዲያብሎሳዊ “ጥበብ” እንዴት እንደተራቀቀ ማጤን ይቻላል፡፡ ጉድ ነው! ወያኔ በዚህች ዓለም የእስካሁንም ይሁን የወደፊት ታሪክ ያልታየና ሊታይም የማይችል የመጀመሪያው ትንግርተኛ ፍጡር ነው፡፡ መጥኔ ለመጨረሻ ዕጣው!
ወያኔን ማንም ያማክረው ማን፣ ማንም ያግዘው ወይ ጃዝ ይበለው ነገር ግን ኢትዮጵያ እንዳታንሠራራ ተደርጋ እየተገደለች ነው – ይህን መረዳት አቅቶናል፡፡ ባለመረዳታችንም የተጣባን ሀገራዊ አባዜ እንደእስከዛሬዎቹ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ወደታሪክ ጎተራ የሚከተት እየመሰለን ተዘናግተናል፡፡ የተናጠል ብልጽግናና ዕድገት ያለ ሀገር ፋይዳ ያለው ይመስል የየግላችንን ሕይወት ለማዳን መራወጣችንን ቀጥለናል፡፡ ይህ ደግሞ ለወያኔ ተመችቶታል፡፡ መቼ ሰው እንደምንሆን ሳስበው አለማሰቤ እንደሚሻለኝ ትውስ ይለኝና ማሰቤ ያስጨንቀኛል፡፡

ወያኔያዊ አገዳደልን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

 

ትምህርትን ገድለውታል፡፡ እዚህና እዚያ ባሉ የግል ትምህርት ቤቶች የሚታዩ ጥቂት ግላዊ ጥረቶችን አትመልከቱ፡፡ የምለው አብዛኛውን ነው፡፡ እናም አብዛኛው የትምህርት ማኅበረሰብ ሞቷል፡፡ በደምብ ነው የሞተው፡፡

ለወትሮው “ስሙን የማይጽፍ ትውልድ” እንል የነበረው ለግነት ነበር፡፡ አሁን ግን በትክክል ስሙን (አስተካክሎ) የማይጽፍ የዲግሪ ተመራቂ በብዛት መታዘብ ተችሏል፡፡ በበኩሌ ይህን አውቃለሁ፡፡ በየኮሌጁና ዩኒቨርስቲው ብንሄድ ተማሪው ይቅርና በርካታው መምህር ራሱ የፊደል ዘር ለመለየት የሚቸገር ነው፡፡ ያጋነንኩ ይመስላል – ግን አይደለም፡፡ ይህ ነው የሚባል የትምህርት ፕሮግራም የሌላቸውና እንዳሻቸው በመፏለል ትውልድን እንዲያመክኑ የተፈደቀላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ እንዳሉ ይነገራል – በተለይ በአጥንትና በደም ለገዢው መደብ የቀረቡ ናቸው ከሚባሉት መካከል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ከአምስትና ስድስት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ የለየላት የማይማን ዋሻ ትሆናለች – ያለጥርጥር፡፡

ማይምነትን ደግሞ አምባገነኖች በጣም ይወዱታል፡፡ ሰጥ ለምበጥ ብሎ ያገኘውን ነገር እንደከብት እያመነዠከ የሚገዛ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው ትምህርትን በመግደል መሆኑን ወያኔን መሰል ሰይጣናዊ አሰለጦች ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ዱላቸው የሚያርፈው ትምህርት ተቋማት ላይ መሆኑ አይገርምም፡፡
ትምህርት የሁሉም ዕድገቶች መሠረት ነው፡፡ በውራጅ የሥነ ሕንጻ ጥበብ መዥጎርጎራችንን አትዩ፤ በከተሞች አካባቢ በሚታዩ የአስፋልት መንገዶች አትታለሉ፡፡ ሕዝበቡን አደንቁረውናል፡፡ ዋናው ስዕል ይህ ነው፤ ያኛው ሽፋን ነው፡፡ በሽፋን ደግሞ መፍረድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሀገራችሁ እየወደመች እንጂ እያደገች እንዳልሆነ በተለይ ዲያስፖራዎች ተረዱ፡፡ ነገ ዞሮ መግያ እያጣችሁ ነው፡፡ የሰው ወርቅ ደግሞ አያደምቅም፡፡ በዚያ ላይ አክራሪነት ዓለምን እያጥለቀለቀ በመጣበት በአሁኑ ሁኔታ ነገና ነገ ወዲያ አሜሪካና አውሮፓ ሦርያና ኢራቅ የማይሆኑበት አጋጣሚ የለም፤ ደግሞም ጀምሯል፡፡ ስለዚህ “ወደ ባዳ አላምጠህ ወደዘመድ ዋጥ ነው”ና ነገሩ ወዳገራችሁ ለመምጣት ማሰባችሁና መገደዳችሁም አይቀርም፡፡ ሀገር ከሌላችሁ ደግሞ የት ትገባላችሁ? ሁሉም ቦታ እሳት ሆነ! እዚህ እየጠፋን ነው – ያለ አንዳች ጦርነት! ሀገርን ለማጥፋት ሥውር ጦርነቶችም አሉ፡፡

Ethiopian_Student_Protest_2001_02ሰሞኑን ለምሳሌ በብዙ ቦታዎች ትምህርት የለም – በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፡፡ የጎረቤቶቼ ልጆች ወደቤታቸው መጥተዋል – ከናዝሬት፣ ከነቀምትና ከደብረ ብርሃን፡፡ ደብረ ብርሃን ሁከት የለም፤ ነገር ግን መምህራኑንና የትምህርቱን አስተዳደር ምን እንደነካቸው አይታወቅም ትምህርት አልጀመሩም፡፡ በብዙ ቦታ ግዴለሽነትና ምንቸገረኝነት ነግሦ የ2ኛው ሴሚስተር ትምህርት ገና አልተጀመረም፡፡ ተማሪውም ግዴለውም፤ መምህሩም ግዴለውም፡፡ ቀጭን ሰበብ እየተፈለገ ትምህርትን መዝጋት በጣም የተለመደ ሆንዋል፡፡ የተማረው ወገን ኮብልስቶን እየፈለጠ ያልተማረው ወገን በዘረኝነትና በጠባብነት መሰላል ተንጠላጥሎ ባንድ አዳር እየበለጸገ ሲታይ በርግጥም የመማር መንፈስን ያጫጫል፡፡ ብዙው ተማሪ ከመማር ይልቅ ዲግሪውን በገንዘብ ቢገዛ ይመርጣል፡፡ ዕውቀት ድባቅ ተመትታ፣ የማወቅ ፍላጎት ተሸመድምዶ እንደምንም ብሎ በሀብት የመክበር ፍላጎት ነው የገነነው – ለገንዘብ ደግሞ አይደለም ባዳን ዘመድንና የገዛ ወላጅንም ሳይቀር መሸጥና አደጋ ማድረስ እጅግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ወያኔ መንፈስንና ኅሊናን እያኮሰመነ ሰውነትን በማወፈር ላይ ይገኛል፡፡ ሰውነት ሲጠበድል ጭንቅላት ይጫጫል፡፡ አእምሮ ሲጫጫ ማመዛዘንና ማስተዋል ገደል ይገባሉ፡፡ ያኔ መተዛዘንና መተሳሰብ ይቀሩና ሰዎች ወደ አውሬነት ይለወጣሉ፡፤ በሀገራችን እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡ ሰውነት በአውሬነት ተለወጠ፡፡ ሃይማኖት ወደሆድ ወርዶ ተሸጎጠ፡፡ በቦሌል በባሌም መክበር ባህል ሆነ፡፡ ገንዘብ ዋጋ አጣ፡፡…

ከፍተኛ የምግብ ዕጥረት አለ፡፡ ምግብ ከሌለ ሰውነት ይጎሳቆላል፡፡ ሰውነት ሲጎሳቆል በትክክል ማሰብ ያስቸግራል፡፡ የሀገራችንን ሕዝብ ስንታዘብ በግምት 98 በመቶው ርሀብተኛ ነው፡፡ ይህ ቁጥር የተጋነነ ይመስላል፡፡ እኔ ግን እላለሁ – ሀብታሞቹም ርሀብኞች ናቸው፡፡ ሁላችንም ተርበናል፤ ሁላችንም ኮስምነናል፡፡
ወንድሞቼና እህቶቼ! ርሀብ ዓይነቱ ብዙ ነው እያልኩ ልፈላሰፍ አምሮኝ እንዳይመስላችሁ፡፤ ወደዚያ ደግሞ አልገባም፡፡ የእንጀራውን ርሀብ ማለቴ ነው፡፡ ሀብታሞቻችን ደናቁርት ናቸው – ብዙዎቹ፡፡ ሌላው ይቅርና የአመጋገብ ዕውቀት እንኳን የላቸውም፡፡ ሀብታም ስለተሆነ የተመጣጠነ ሣይንሣዊ አመጋገብን በአግባቡ ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አዳር ከብሮ የሚያድር ሰው በአንድ አዳር አውቆ አያድርምና በገንዘቡ እየጠጣ በሽታ ይገዛበት እንደሆነ እንጂ ስለአመጋገብ አንድም መጽሐፍም ሆነ ባለሙያ አያማክርም – አብዛኛው ሀብታም ከፊደል ዘር ጋር የተኮራረፈ መሆኑ ደግሞ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ሥጋና ዊስኪ ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ይተካል እንደማትሉኝ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም እሱም እንደኛው ርሀብተኛ ነው – የኛን ባያህልም፡፡ ያለ ዕውቀት የሚገኝ ገንዘብ ከጠላት ተለይቶ አይታይም ወንድሞቼ፡፡

ስለሆነም የኛ የድሆቹ ርሀብ መሠረቱ ዕውቀትም ሀብትም ሲሆን የሀብታሞቹ ርሀብ መሠረት ግን በዋናነት አላዋቂነት ነው፡፡ ተመልከት – ሥጋ፣ ቅቤ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ወተት፣ ዕንቁላል፣ ዓሣ፣ ወዘተ. መቼና በስንት መጠን ሰውነታችን ማግኘት እንዳለበት በጥናት የተደረሰበት ነገር አለ፡፡ ገምቢ ምግቦች፣ ኃይል ሰጭ ምግቦች፣ ከበሽታ ተከላካይ ምግቦች፣ ቪታሚኖቾ ወዘተ. የሚሏቸው አሉ፡፡ ድሃው አንዴውኑ ይበልጡን ከሀብትና ከዚሁ ባልተናነሰም ከዕውቀት ስለተፋታ ይህ የተመጣጠነ ምግብ ነገር ሲነሣ አያሳስበውም፡፡ …

በርሀብ የሚገረፍ ድሃ ሕዝብ ሞቱን ተሸክሞ ይዞራል፡፡ ስለሀገርና ስለወደፊት የሚያስብበት አእምሯዊ ጫንቃም የለውም፡፡ ሕዝቡን እዩት – በተለይ በገጠር፡፡ ልብሱ እላዩ ላይ አልቆ እየተንጠራወዘ ሲሄድ ታያላችሁ፡፤ ወያኔ ለዚህ አበቃን፡፡ የተራበን ሕዝብ ከታዛዥ እንስሳ የቤት መለየት ያስቸግራል፡፡ አመጋገብህ አስተሳሰብህን ይወስናል፡፡ የአስተሳሰብ ችሎታህ በምግብህ ይመሠረታል፡፡ አሸር ባሸር በልተህ እንደጤናማ ሰው ላስብ ብትል አትችልም፡፡ የምትመገበው የማይረባ የመሆኑን ያህል የምታስበውም ውዳቂ ነው፤ በአካል ማደግ፣ በትምህርት ደረጃ መላቅ እዚህ ላይ ዋጋ የላቸውም፡፡ በሚገባ ያልተመገበ ዶክተር እንደሕጻን ሰኞ ማክሶኞ ሲጫወት ብታገኘው ብዙም አትደነቅ፤ አትዘንበትም፡፡ እናም ወያኔዎች ዱሮ ለከብቶቻችን እንኳን ስንሰጥ ከብቶቻችን የሚያሳዝኑንን የጓያ ሽሮ አሳጥተውን በርሀብና በእርዛት እየፈጁን ናቸው፡፡ ሀገርን መግደል ከዚህ በላይ የለም፡፡ ውኃም የለም፤ መብራትም ይቆራረጣል፡፡ ህክምና ዜሮ ነው፡፡ ሀኪምም የለም፡፡ ሀኪሙ በዕውቀት ዜሮ ነው፡፡ አዋላጅ የለም፤ ምን አለፋችሁ ኑሯችን በውር ድምብር ነው፡፡ መንግሥት ያለን ስለመሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በኪነ ጥበቡ ነግቶ ይመሽልናል፡፡
ሙስናው ጫፍ ደርሷል፡፡ ባዶ እጅህን ይዘህ የትም ቦታ ጉዳይ አይፈጸመልህም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳን ብትሄድ ይሄው ነው፡፡ ከአንድ ብዙም ጥቅም ከሌለው(ያው በሙስና ነው) ደብር ወደሌላ ለመዛወር ለአበው ካህናትና ለአኃው ዲያቆናት ባለሥልጣናት በብዙ ሺህ የሚገመት ጉቦ ከፍለህ ነው የሚሳካልህ፡፡ የዱሮውን ጋዜጠኛ የአሁኑን የቤተ ክርስቲያን ካድሬ እንደልቡ የማነ ዘመንፈስን የቅርብ ጊዜ የሙስና ታሪክ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ሞተናል በቁም፡፡
በየቦታው የመንግሥት ሥራ በቅጡ አይሠራም፡፡ ቢሮዎች ዝግ ናቸው – ስብሰባ፣ ስብሰባ፣ ስብሰባ፤ የማያልቅ ስብሰባ፡፡ አብዛኛው ስብሰባ ውሸት ነው፡፡ ሰውዬው ከቢሮ ወጥቶ የግል ቢዝነሱን ሲያቀላጥፍ ጸሐፊው “ስብሰባ ላይ ናቸው” የሚል ታፔላ አፏ ይለጠፍላትና እንደበቀቀን “የሥራ ሂደት ባለቤቱ ኃላፊ ስብሰባ ላይ ናቸው“ ስትል ትውላለች፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ያለው መዋቅራዊ ቅርጽና የተለጠፈው የመፈክርና የመልካም ሥነ ምግባር መርሆ ዓይነት ብዙና እጅግ ማራኪ ይመስላል – ውስጡ ግን ባዶ ነው፡፡ ሁሉም የውሸትና የታይታ ነው፡፡ ያው ቢያንስም ደሞዝ መብያ እንጂ ሥራን በአግባቡ የሚሠራ ሠራተኛና ቢሮ አለ ማለት አይቻልም፡፡
ምን ይብቃን? በትምህርት ዜሮ፣ በሃይማኖት ዜሮ፣ በሞራል ዜሮ፣ በሥራ ዜሮ፣ በምግባር ዜሮ፣ በሁሉም ዜሮ ….. ሆነናል፡፡ ማን ነው ይህችን ሀገር የሚረከበው? የወጣቱን መንፈስ አሽመድምደውታል፤ አብዛኛው የማይበርደው የማይሞቀው ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ በልዩ ልዩ ተደራቢ ባሕርያትና ሱሶች ተጠምዶ እንኳንስ ሀገሩን ራሱንም የረሳው ዜጋ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከየትኛው ሰማይ የሚላክ ዜጋ ይሆን ነፃነታችንን የሚያላብሰን? አንዳንችን ሌላኛችንን ነፃ እንድናወጣ ከተጠበቀስ መቼ ነው ነፃ የምንወጣው? የኔንስ ተውት የልጆቼና የልጅ ልጆቼ ዕጣ ምን ይሆን? ላብድ ነው፤ ጨነቀኝ – ባብድ ይሻል ይሆን? እስኪ የሞከራችሁት ካላችሁ ንገሩኝ – በተረቱም እኮ “ካላበዱ ወይ ካልነገዱ” ነው የሚባል፡፡ ብቻ አንዳች አዋጭ መፍትሔ ያላችሁ ጠቁሙኝ፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት በእስካሁኑ ሁኔታ የበሬ ቆለጥ ሆና የቀረች ትመስላለች- ቀበሮዋ ስትከተል ውላ ምራቋን የጨረሰችባት ቆለጥ፡፡ የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ሥልትም ሥራውን በሚገባ እየሠራ ነው – ጥቂት የማይባሉ ባንቱስታዎችን ፈጥሮ ለተጨማሪ ዓመታት ወደ አረንቋ ሊከቱን እየተሟሟቁ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ያስጨንቃል – ካለፈውና ካለው ይልቅ የወደፊቱም በእጅጉ ይዘገንናል፡፡ ምን ይዋጠን? ራሳችሁን ጠይቁና እናንተም እንደኔው ጥቂት ተጨነቁ፡፡ ለመጨነቅ ደግሞ ለሀብትና ለዝና ወይም ለትምህርት ደረጃችሁ ወይም ለዕድሜያችሁ ሥፍራ ብዙም አትስጡ፡፡

Advertisements

Discussion

No comments yet.

Give a comment

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

facebook

https://www.facebook.com/

Blog Stats

  • 54,675 hits
Advertisements
%d bloggers like this: